አብዮተኛው ቼ ጉዌቫራ የተወለደባት ቤት ለገበያ ቀረበች

ቼጉቬራ የተወለደበት የአርጀንቲናዋ ግዛት ሮዛሪዮ የሚገኘው ህንፃ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቼ ጉዌቫራ የተወለደበት የአርጀንቲናዋ ግዛት ሮዛሪዮ የሚገኘው ህንፃ

የግራ ዘመሙ አብዮተኛ የቼ ጉዌቫራ የትውልድ ቤት ለሽያጭ ቀረበ።

የ20ኛው ክፍለ ዘመን አብዮተኛ ኤርነስቶ ቼ ጉዌቫራ የተወለደበት ቤት ለሽያጭ የቀረበው በአርጀንቲና ሮዛሪዮ ከተማ ነው፡፡

አሁን የቤቱ ባለቤት የሆነው ሰው ፍራንሲስኮ ፋሩጊያ ይባላል፡፡ ይህንን ታሪካዊ ቤት ገዝቶት የነበረው በነርሱ አቆጣጠር በ2002 ዓ. ም ነበር፡፡

ቼ የተወለደባት ይቺ 240 ካሬ የሆነች አፓርታማ በዓለም ላይ ልዩ ቦታ ከሚሰጣቸው መኖርያ ቤቶች አንዷ ናት፡፡

ልዩ ቦታ ያሰጣትም የአብዮተኛው የቼ ኩቬራ የትውልድ ቤት በመሆኗ ነው፡፡

የቤቱ ባለቤት የቼን የትውልድ ቤት የባሕል ማዕከል ለማድረግ ሞክሮ አልተሳካለትም፡፡

ይህ አሁን ቤቱን ለገበያ ያቀረበው ነጋዴ ቤቱ የሚሸጥበትን ዋጋ ተመን ገና ይፋ አላደረገም፡፡

በሮዛሪዮ ከተማ እምብርት ላይ ኡርኩዛ እና በኢንትሬ ራዮስ በሚባሉ ጎዳናዎች መሀል የሚገኘው ይህ አፓርታማ ህንጻ ባለፉት ዓመታት በጎብኚዎች የሚዘወተር ስፍራ ነበር፡፡

የቼ ጉዌቫራን የትወልድ ቤት ከጎበኙ ታዋቂ ሰዎች መሀል የዩራጓዩ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆዜ ፔፔ እና የፊደል ካስትሮ ልጆች ይገኙበታል፡፡

ምናልባትም የዚህ ቤት ታሪካዊ ጎብኚ ተብለው ከተጠቀሱት ሰዎች መሀል አልቤርቶ ግራናዶስ ይገኝበታል፡፡

ቼ ኩቬራ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

አልቤርቶ ከራሱ ከቼ ጉዌቫራ ጋር ድሮ ወጣት ሐኪም ሳለ በ1950ዎቹ በደቡብ አሜሪካ አገራት በሞተር ሳይክል ተጉዘው ነበር፡፡

በኛ አገር የግራ ዘመም ፖለቲካ ውስጥ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ቼ ኩቬራ የተወለደው እንደ ጎርጎሳውያኑ በ1928 በአርጀንቲና ነበር፡፡

ለጭቁኖች መብትና ነጻነት ሲታገል የኖረው ቼ የተወለደው እጅግ የተደላደለ ኑሮ ከሚመራ ሀብታም ቤተሰብ ነው፡፡

ነገር ግን በኋላ ላይ በደቡብ አሜሪካ አገራት በተለይም በቺሊ፣ በፔሩና በቪኒዝዌላ የተመለከተው ድህነትና ጭቆና ለትግል እንዳነሳሳው ይነገራል፡፡

ከ1953 እስከ 1959 (እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር) የተካሄደውን የኩባ አብዮትን ከፊት ከመሩት ሰዎች አንዱ ቼ ጉዌቫራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በዚህ አብዮት የዚያን ዘመኑ የኩባ አምባገነን ፉልጌንቺዮ ባቲስታ ከመንገበራቸው ተፈንግለዋል፡፡

ቼ ከዚህ ስኬታማ አብዮት በኋላ አርፎ አልተቀመጠም፡፡ ይባስ ብሎ ድንበር እየተሻገረ ለጭቁኖች ትግል ራሱን ሰጠ፡፡

ሌሎች የደቡብ አሜሪካና በመላው ዓለም የሚገኙ ጭቁን ሕዝቦችን ነጻ ለማውጣት ቆርጦ ተነሳ፡፡

ከኩባ ተነስቶ ወደ ቦሊቪያ በመሻገር በያኔው ፕሬዝዳንት ሬን ባሬንቶስ ላይ አመጽ ቀሰቀሰ፡፡

በመጨረሻ በአሜሪካ ልዩ እርዳታ የቦሊቪያ ጦር ቼ ኩቬራን ከነ ግብረአበሮቹ በቁጥጥር ሥር አዋለ፡፡

እንደ ጎርጎሳውያኑ በጥቅምት 9፣ 1967 ላ ሂጓራ በምትባል ገጠር ውስጥ ተገደለ፤ ሬሳው የተቀበረውም ምስጢራዊ በሆነ ቦታ ነበር፡፡

ከተገደለ ከ30 ዓመታት በኋላ በ1997 ቼ የተቀበረበት ምስጢራዊ ስፍራ በመታወቁ ሬሳው ወደ ኩባ ተመልሶ በክብር በድጋሚ እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡

ቼ አሁንም ድረስ በዓለም ሕዝቦች መሀል በሁለት አጽናፍ የሚታይ አወዛጋቢና ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው ነው፡፡

አፍቃሪዎቹ አብዮተኛና ድንበር ያልገደበው ለሰው ልጆች ሁሉ የታገለ የጭቁኖች አባት አድርገው ሲመለከቱት ሌሎች ደግሞ ጨካኝና ጨፍጫፊ አድርገው ይስሉታል፡፡