የአሜሪካ ምክር ቤት፡ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ከቀሰቀሱት ግርግር ጋር በተያያዘ አራት ሰዎች ሞቱ

የትራምፕ ደጋፊዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል

ዋሺንግተን ውስጥ የተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች የአገሪቱን ምክር ቤት ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ በተፈጠረ ፍጥጫ አራት ሰዎች መሞታቸው ተነገረ።

ካፒቶል ሒል በተባለው የምክር ቤቱ ህንጻ ላይ በተቃዋሚዎቹ በተፈጸመው ወረራና ተከትሎት በተፈጠረው ግጭትና ግርግር በቀዳሚነት አንዲት ሴት በፖሊስ ተተኩሶባት እንደሞተች የተዘገበ ሲሆን፤ ኋላ ላይ ደግሞ ተጨማሪ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

ከሞቱት በተጨማሪ አስካሁን ድረስ ከ50 በላይ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 47ቱ የተያዙት የተጣለውን የሰዓት እላፊ ገደብ በመጣሳቸው ነው ተብሏል።

ከዚህ ባሻገር ቢያንስ 14 የሚደርሱ የፖሊስ አባላት ላይ የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከመካከላቸው ሁለቱ ሆስፒታል መግባታቸው ተነግሯል።

ወራራ በአሜሪካ ምክር ቤት ላይ

በዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ የሆነው የካፒቶል ሒል ግዙፍ ህንጻ ላይ የትራምፕ ደጋፊዎች ወረራ ፈጽመው ለሰዓታት ግርግር ተፈጥሮ ነበር።

ይህ በአሜሪካ ውስጥ ይሆናል ተብሎ የማይጠበቅ ድርጊት የተፈጸመው ከሰዓታት በፊት ነው።

የዶናልድ ትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች ካፒቶል ሒልን ከተቆጣጠሩ በኋላ ንብረት ሲያወድሙና ለፕሬዝዳንቱ ያላቸውን የማይናወጽ ፍቅር ሲገልጹ ተስተውለዋል።

ካፒቶል ሒል የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ ሲሆን የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት በቀኝ፣ የሕግ መምሪያው ምክር ቤት መሰብሰቢያ ደግሞ በግራ በኩል የሚገኝበት፣ በርካታ ቢሮዎች ያሉበት ታሪካዊ ሕንጻ ነው።

ሕንጻው ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረ ነው።

የአገሪቱ ሕዝብ እንደራሴዎች ተሰብስበው ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የምርጫ ውጤት ዙሪያ በመነጋገር ላይ ሳሉ ነው በድንገት በሺህ የሚቆጠሩ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ምክር ቤቱን ሰብረው የገቡት።

ትዕይቱን ለዓለም በቀጥታ ያስተላልፉ የነበሩ የዜና ማሰራጫዎች ድርጊቱን ማመን ተስኗቸው ለሰዓታት ፕሮግራማቸውን አጥፈው ነውጡን አሰራጭተዋል።

ይህ ያልተጠበቀ ክስተት በሚሆንበት ጊዜ ስብሰባ ላይ የነበሩ የሕዝብ እንደራሴዎች በፖሊስ ታጅበው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል።

በተቀሰቀሰው ግርግር ሳቢያ የዋሺንግተን ከንቲባ በከተማዋ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥለዋል። የካፒቶል ሂል አካባቢም ሙሉ በሙሉ ዝግ እንዲሆን ተደርጓል።

ተቃዋሚዎች በምክር ቤቱ ግቢ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዶናልድ ትራምፕ መጀመሪያ አካባቢ ደጋፊዎቻቸውን ድርጊቱን እንዲገፉበት የሚያበረታቱ መልዕክቶችን እየላኩ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ግን ሰላማዊ እንዲሆኑና ወደቤታቸውም እንዲሄዱ የሚያሳስብ መልዕክትን አስተላልፈዋል።

የሕግ መምሪያውና የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት በአንድ ተሰብስበው በሚነጋገሩበት ወቅት ነውጥ በመነሳቱ የጆ ባይደንን ፕሬዝዳንታዊ ድል የማጽደቁን ውይይት ለጊዜ ተቋርጦ ነበር።

በዚህ ዓለምን ጉድ ባሰኘ ነውጥ አራት ሰው መሞታቸው የተዘገበ ሲሆን በርካታ የጸጥታ አስከባሪዎችም ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር ሲሞክር ታይቷል።

ነውጠኞቹ በተደጋጋሚ "ምርጫው ተጭበርብሯል" እንዲሁም "ዶናልድ ትራምፕ ይምራን" የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር።

የምሽቱ አስደናቂ የሆነው ክስተት ወደ አዳራሹ በኃይል ጥሰው ከገቡት ተቃዋሚዎች አንዱ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት በሚቀመጡበት የሴኔት ሸንጎ ወንበር ላይ እግሩን ሰቅሎ መታየቱ ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ በመጨረሻ በቪዲዮ ባስተላለፉ መልዕክት ለደጋፊዎቻቸው "ሕመማችሁ ይሰማኛል፤ ምንኛ እንደተጎዳችሁ ይገባኛል። በቃ አሁን ወደቤት መሄድ ነው ያለባችሁ። ሰው እንዲጎዳብን አንፈልግም" ብለዋቸዋል።

ጆ ባይደን በቴሌቪዥን ቀርበው በቀጥታ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር"በአሜሪካ ዲሞክራሲ ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል" ብለዋል። ተቀናቃኛቸው ትራምፕም በአስቸኳይ ወጥተው ውንብድና ላይ ያሉ ደጋፊዎቻቸውን አደብ እንዲያሲዙ ጠይቀዋል።

ካፒቶል ሒል በነውጥ ላይ እያለ ከዋሺንግተን ዲሲ በሚጎራበቱ ግዛቶች የአሜሪካ ወታደሮች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ሆነዋል። የካፒቶል ሒል ፖሊሶችን ለመደገፍም ኤፍቢአይ ወደ ስፍራው ተሰማርቷል።

በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችም ነውጡ ከተስፋፋ በሚል ከፍተኛ ፍርሃት እንደረበበ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው።

የጸጥታ ኃይሎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters