የአሜሪካ ምክር ቤት፡ ደጋፊዎቻቸው የአገሪቱ ምክር ቤትን ከወረሩ በኋላ ትራምፕ ከትዊተርና ከፌስቡክ ታገዱ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለተቃዋሚ ሰልፈኞቹ መልዕክት ሲያስተላልፉ

የፎቶው ባለመብት, N/A

ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዋነኛዎቹ የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች እንዲታገዱ ሆነዋል።

ይህ እርምጃ የተወሰደባቸው ደጋፊዎቻቸው የካፒቶል ሂል ግቢን መውረራቸውና አደጋ ማድረሳቸውን ተከትሎ ነው።

ዓለምን ባስገረመውና በአሜሪካ ምድር ይሆናል ተብሎ ባልተጠበቀ ነውጥ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች የታችኛውና የላይኛው ምክር ቤት መሰብሰቢያ የሚገኝበትንና የመንግሥት መቀመጫ የሆነውን ካፒቶል ሒልን ጥሰው በመግባት አደጋ ያደረሱት ከሰዓታት በፊት ነው።

ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎቻቸውን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠንካራ መልእክት ያስተላልፋሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ሰዓት 'እወዳችኋለሁ' የሚል መልእክት አስተላልፈዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን የተለመደውን ምርጫው ተጭበርብሯል የሚለውን ያልተጨበጠ ክስም በማኅበራዊ ገጻቸው አስተላልፈዋል።

ትዊተር ሦስት የትራምፕ መልእክቶችን ከገጹ እንዲወገዱ እንደጠየቀ ይፋ ያደረገ ሲሆን ከፖሊሲያችን ጋር የሚጻረሩ መልእክቶች ስለሆኑ ነው መወገድ ያለባቸው ብሏል።

ካልተወገዱ ግን ትራምፕን እስከመጨረሻው ከትዊተር አሰናብታቸዋለሁ ብሏል።

ይህም ትዊተር ዶናልድ ትራምፕን እስከመጨረሻው ለማሰናበት በርካታ ቀናትን ላይጠብቅ ይችላል ማለት ነው።

የትዊተር ውሳኔ በእንዲህ ሳለ ፌስቡክ በበኩሉ ትራምፕን ለ24 ሰዓታት እግድ ጥሎባቸዋል። ዩትዩብ በበኩሉ የትራምፕን ቪዲዯዎች ከገጹ እንዲወርዱ አድርጓል።

ፌስቡክ ለምን ትራምፕን ለ24 ሰዓታት ከገጹ እንዳገደ በገለጸበት መግለጫው ምክንያቱም እየታየ ላለው ነውጥ ትራምፕ ማባባስ እንጂ ማብረድ ባለመቻላቸው ነው ብሏል።

የትራምፕ ደጋፊዎች የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ የሆነውን ካፒቶል ሒልን ሰብረው በመግባት ከፖሊስ ጋር የተጋጩ ሲሆን በዚህ ዓለምን ጉድ ባሰኘው ነውጥ የአንዲት ሴት ሕይወት ማለፉም ተነግሯል።

የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ሒልን ጥሰው ጥቃት ሲፈጽሙ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት በጆ ባይደን ጉዳይና ድል እየተከራከረ ነበር።

በሁለቱ ምክር ቤቶች ሪፐብሊካኖችና ዲሞክራቶች የኖቬምበሩን የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉትን ጆ ባይደንን ውጤት ማጽደቅና አለማጽደቅ ላይ እየተነጋገሩ በነበረበት ሰዓት ነው የትራምፕ ደጋፊዎች ያልተጠበቀ እርምጃ የወሰዱት።

ይህ ነውጥ ከመከሰቱ በፊት ትራምፕ በዋሺንግተን ናሸናል ሞል ለደጋፊዎቻቸው ምርጫው ተዘርፏል ሲሉ ነበር።

ይህ ከሆነ ከሰዓታት በኋላ ደጋፊዎቹ ካፒቶል ሒልን ጥሰው ገብተው ጉዳት ማድረስ ጀመሩ። ትራምፕ ድርጊቱን ያወግዛሉ ሲባል በቪዲዯ ቀርበው ምርጫው ተጨበርብሯል የሚለውን ንግግር ደገሙት። ይህ አልበቃ ብሎም ነውጠኞቹን እወዳችኋለሁ። ጀግኖች ናችሁ ያልዋቸው።

ዩ ትዩብ ይህንን የፕሬዝዳንቱን ንግግር የኔን ፖሊሲ የማይከተል ስለሆነ አስወግጄዋለሁ ብሏል።

ትዊተር በበኩሉ ይህንን ቪዲዮ ከማስወገድ ይልቅ ሰዎች እንዳያጋሩት እና መውደዳቸውን የሚያሳየውን ምልክት (ላይክ እንዳያደርጉት)፣ ከቪዲዯው ሥር አስተያየት እንዳይሰጡ በማድረግ የቪዲዯ መልእክቱ እንዳይዛመት አድርጎ ነበር።

በኋላ ላይ ግን ቪዲዯውን ሙሉ በሙሉ አስወግዶ ፕሬዝዳንቱም ለጊዜው ከትዊተር እንዲሰናበቱ አድርጓቸዋል።

ካፒቶል ሒልን የመውረሩ የነውጥ እንቅስቃሴ ሲስተባበር የነበረው በዋናነት እነዚህኑ ማኅበራዊ የትስስር መድረኮችን በመጠቀም ነበር።