ኮሮናቫይረስ፡ በአፍሪካ ሁለተኛው ዙር የኮቪድ ወረርሽኝ "በጣም ፈጣን ነው" ተባለ

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን ማድረግ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ወሳኝ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አፍሪካን በሁለተኛ ዙር እያጠቃ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከመጀመሪያው ይልቅ "እጅግ ፈጣን" መሆኑን የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ገለፀ።

የድርጅቱ ኃላፊው፣ ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አፍሪካ በአሁን ሰዓት በቀን 30 ሺህ በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎችን እያስመዘገበች መሆኑን ገልፀው፣ ይህ ግን በሐምሌ ወር አጋማሽ በቀን 18 ሺህ ሰው ብቻ እንደነበር በማነጻጸር ቫይረሱ በፍጥነት እየተሰራጨ መሆኑን እንደሚያሳይ አብራርተዋል።

አፍሪካ በአሁኑ ሰዓት ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ስታረጋግጥ ከእነዚህም መካከል 68,755 ያህሉ ደግሞ መሞታቸውን ይፋ ተደርጓል።

ሩዋንዳ፣ ናሚቢያ፣ ዚምብብዌ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አዲስ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥለዋል።

ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ባለበት ለማቆምና ለመግታት የአህጉሪቷ ብቸኛ ተስፋ የአፍና አፍንጫ መሸፈናን በአገገግባቡ ማድረግ ብቻ ነው ካሉ በኋላ መንግሥታት ድጎማ በማድረግ ለሕዝባቸው እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ አህጉር በሚገኙ የተለያዩ አገራት የሚኖሩ ሕዝቦች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሁልጊዜ አልያም ፈጽሞውኑ እንደማያደርጉ የገለጹት ዶክተሩ፣ የአካላዊ ርቀቱም ቢሆን እጅግ በጣም የተጠጋጋ መሆኑን ማስተዋላቸውን ገልጸዋል።

"ይህ አሳሳቢ ነው" ካሉ በኋላም፣ "ሁለተኛው ዙር እጅግ ፈጣን ነው" ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።