የተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሱዳን እየመጡ ነው አለ

አዲሱ የስደተኞች ካምፕ

የፎቶው ባለመብት, UNHCR/Taylan Dagci

የምስሉ መግለጫ, አዲሱ የስደተኞች ካምፕ

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) አሁንም ስደተኞች ከኢትዮጵያ የትግራይ ክልል እየመጡ መሆኑን ሲያስታውቅ በቅርቡ ወደ ሱዳን ከተሰደዱት ሰዎች መካከል የመጀመሪያዎቹን ወደ አዲስ የስደተኞች ማቆያ ማዘዋወሩን ገለጸ።

የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በገባ በጥቂት ቀናት ውስጥ 800 የሚደርሱ ሰዎች ድንበር ተሻግረው ወደ ምሥራቃዊ ሱዳን የገቡ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ፤ ከኅዳር ወር ጀምሮ ከ56 ሺህ በላይ ስደተኞች ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን አስታውሷል።

በቅርቡ የደረሱት ስደተኞች በጦርነት መካከል መንቀሳቀስ ሳይችሉ የቆዩ፣ በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ጥቃት የደረሰባቸውና ቤታቸው የተዘረፈ፣ ያለፈቃዳቸው ለውትድርና የተመለመሉ አዋቂ ወንዶችና ልጆች እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃት ያጋጠማቸው ሴቶችና ልጃገረዶች ይገኙባቸዋል።

ድርጅቱ መግለጫ ላይ እንዳለው ወደ ሱዳን የደረሱት አዲሶቹ ስደተኞች ከያዟቸው ጥቂት ልብሶች ውጪ ምንም የሌላቸው ሲሆኑ፤ ለቀናት ባደረጉት ጉዞ የተጎሳቆሉና የደከሙ ናቸው ሲል ገልጿል። ከመካከላቸው ከ30 በመቶ የሚበልጡት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ሲሆን 5 በመቶው ደግሞ ከ60 ዓመት በላይ ናቸው።

ኡምራኩባ የተሰኘው የስደተኞች ጣቢያ ሊሞላ መቃረቡን የገለጸው ዩኤንኤችሲአር ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በድንበር ላይ ካሉ የመቀበያ ቦታዎች ስደተኞቹን ከገዳሪፍ ከተማ 136 ኪሎ ሜትሮች ርቆ ወደ የሚገኘው አዲስ ወደ ተከፈተው ቱናይድባህ በፍጥነት ለማዘዋወር እየጣረ መሆኑንም ገልጿል።

የስደተኞች መቀበያ ቦታዎቹ በበርካታ ሰዎች የተጨናነቁና ለድንበር ቅርብ በሆኑ ቦታዎች ላይ ስላሉ የስደተኞቹ ደኅንነትን ስጋት ውስጥ የሚጥሉ ናቸው ብሏል።

ድርጅቱ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ቁጥራቸው እየጨመረ ያለውን የስደተኞች ለማስተናገድ ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክቷል። በአሁኑ ጊዜ ከ20 በላይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለስደተኞቹ መጠለያ፣ ምግብና የጤና አገልግሎት በማቅረብ በአጋርነት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሷል።

ድርጅቱ በስደተኞቹ ካምፕ ውስጥ በጣሙን የሚያስፈልጉትን የውሃና የንጽህና መጠበቂያ አቅርቦቶችን እንዲሁም የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ለማከናወን ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ገልጿል።

በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት ማብቂያ ላይ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ለሚያስፈልገው የአሰቸኳይ ጊዜ ሥራ ዩኤንኤችሲር 40 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ቃል የተገባለት ቢሆንም ይህ ድርጅቱ በሱዳን፣ በኢትዮጵያና በጂቡቲ ለሚያደርገው ድጋፍ 37 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን ነው ተብሏል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል ውስጥ በተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን መሰደዳቸው የተነገረ ሲሆን፤ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑት ደግሞ በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ገልጸዋል።