ኮሮናቫይረስ ፡ ቻይና የኮቪድ-19 መነሻን የሚመረምሩ ባለሙያዎችን ቪዛ በመከልከሏ ዶ/ር ቴድሮስ ቅሬታ አሰሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ቻይና ለዓለም ጤና ድርጅት ለላካቸው የመርማሪ ሳይንቲስቶች ቡድን ቪዛ መከልከሏ አሳዛኝ እንደሆነ በመግለጽ ቅሬታቸውን ገለጹ።
ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የዓለም ጤና ድርጅት አንድ የመርማሪዎች ቡድን ወደ ቻይና ለመላክ ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ነበር። ቡድኑ ኮሮናቫይረስ ተነስቶባታል የምትባለው ዉሃን ከተማ ገብቶ በትክክል የተህዋሲውን መነሻ ለማወቅ ምርመራ ለመጀመር ነበር ትልሙ።
ሆኖም ቻይና ባልታወቀ ምክንያት ለዚህ ቡድን የመግቢያ ቪዛ ሳታዘጋጅ ቀርታለች። የመርማሪ ቡድኑ ሁለት አባላት ጉዞ ጀምረው የተመለሱ ሲሆን አንዱ ደግሞ በሦስተኛ አገር ትራንዚት በማድረግ ላይ እያለ ነው ዜናው የተሰማው።
የዓለም ጤና ድርጅት መርማሪ ቡድኑ ቻይና መግባት ያልቻለው ከቪዛ ጉዳይ በተያያዘ ነው ብሏል።
ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ይህ አጣሪ ቡድን ወደ ቻይና የማምራት ጉዳይ ላይ ስምምነት የተደረሰው ባለፈው ታኅሣስ ነበር። እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ የዓለም ጤና ድርጅት ከቻይና ጋር ረዥም ድርድር ማድረጉ ታውቋል።
ተህዋሲው መጀመሪያ ተገኘ የተባለው በፈረንጆቹ 2019 መጨረሻ አካባቢ ሲሆን መነሻውም ቻይና ውስጥ የሚገኝ የእንሰሳት መሸጫ ገበያ ውስጥ ነው የሚል መላምት አለ።
የዓለም ጤና ድርጅት አለቃ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ቻይና የቪዛ ጉዳይን በጊዜ ማጠናቀቅና ማሟላት ባለመቻሏ "ከፍ ያለ ቅሬታ" እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ሁለቱ የመርማሪ ቡድን አባላት ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ሌሎች ደግሞ ጉዞ በሚጀምሩበት ቅጽበት የመግቢያ ቪላ አለመዘጋጀቱ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።
"ቻይና ይህ ሂደት በፍጥነት እንደሚሟላ አረጋግጣልን ነበር" ሲሉ በጄኔቫ ለጋዜጠኞች የተናገሩት ዶክተር ቴድሮስ የመግቢያ ቪዛው አለመድረሱን አስመልክቶ ከቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገሩበት እንደሆነ እና ይህ ቡድንና ተግባሩ ለጤና ድርጅቱም ሆነ ለዓለም ኅብረተሰብ ቅድሚያ የሚሰጠው ዐቢይ ጉዳይ ነው ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ወደ ዉሃን ከተማ ሊልካቸው የነበሩት 10 ዓለም አቀፍ የጤና አዋቂዎች ቡድን አባላትን ሲሆን የመርማሪ ቡድኑ አባላት ዋንኛ ተግባር የሚሆነው ተህዋሲው የተነሳበትን ሁነኛ ቦታና ሁኔታ ማመላከት ነበር ተብሏል።
ተህዋሲው እንዴት ከእንሰሳት ወደ ሰው ተላለፈ የሚለውም ምላሽ ያገኛል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
ባለፈው ዓመት ምርመራው በዚህ በያዝነ ው የፈረንጆች የመጀመሪያ ወር የመጀመሪያ ቀን ይጀመራል ተብሎ ስምምነት ተደርሶ ነበር።
ከ10ሩ የምርመራ ቡድን አባላት ሁለቱ ትናንት ማክሰኞ ጉዞ ጀምረው የነበረ ሲሆን አንዱ በሦስተኛ አገር በትራንዚት ላይ እያለ ነው የመግቢያ ቪዛ እንደማትሰጥ ቻይና የገለጸቸው ተብሏል።
በ2019 በሁቤይ ግዛት ዉሃን በተባለ ከተማ ነበር የኮቪድ-19 ተህዋሲ መጀመሪያ በሰው ልጅ ላይ የተገኘው።
ዉሃን ከሚገኘው ከእንሰሳት ገበያ ወደ ሰዎች ተህዋሲው ተሸጋግሯል ብለው የሚያምኑ እንዳሉ ሁሉ ተህዋሲው ከቤተሙከራ አፈትልኮ ወጥቶ ነው ወደ ሰው የተዛመተው ብለው የሚገምቱም አልጠፉም።
አንዳንዶች ደግሞ ይህ ተህዋሲ በሌሊት ወፍ ውስጥ ለዘመናት ኖሮ የቆየና በኋላ ላይ ወደ ሰዎች የተላለፈ ቫይረስ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
ቴድሮስ አድሃኖም የሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት ሊልካቸው የነበሩት 10 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ምርመራ ለማድረግ ነበር ወደ ቻይና ለመጓዝ ያቀዱት።
ተህዋሲው ከተከሰተ ጀምሮ ከ86 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በዓለም ዙሪያ አጥቅቶ ከ1 ሚሊዮን 800 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ደግሞ እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል።







![ኮሮናቫይረስን ማደን [ስዕል]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/660/cpsprodpb/2642/production/_112749790_01_investigation_01_hd.jpg.webp)








