አሜሪካ፡ የትራምፕ ሥልጣን ዘመን ማብቃትና 25ኛው አሜንድመንት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ የቀራቸው ከሁለት ሳምንታት ያነሰ እድሜ ብቻ ነው።
ነገር ግን በትናንትናው ዕለት ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸው የመንግሥት መቀመጫና የሁለቱ ምክር ቤቶች አዳራሾች የሚገኙበትን ግዙፉን የካፒቶል ሒል ህንጻን ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ ከፍተኛ የሴኔት ምክር ቤት አባላት ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን እንዲባረሩ እየጠየቁ ነው።
ለዚህም የአሜሪካ ሕገመንግሥት 25ኛው አሜንድመንት [ማሻሻያ] እየተጠቀሰ ነው። ይህ ማሻሻያ አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አካላዊ ወይም አእምሯዊ ጤና ከራቀው ምክት ፕሬዝዳንቱ ቦታውን በተጠባባቂነት ተረክቦ አገሪቱን እንዲመራ ያዛል።
ሆኖም ይህ እንዲተገበር የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲን ጨምሮ በትንሹ 8 የካቢኔ አባላት በጉዳዩ ላይ መስማማት አለባቸው። ነገር ግን ይህ የመሆን እድሉ ለጊዜው ጠባብ ነው ተብሏል።
የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች ካፒቶል ሒልን ጥሰው ሲገቡ ታህታይና የላዕላይ ምክር ቤት አባላት የባይደንን መመረጥ ከግዛት ተወካዮች የማረጋገጥ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ይህንኑ በመካሄድ ላይ ነበሩ።
አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲና ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስም በሸንጎ ላይ ተገኝተው ነበር።
ይህንን ለአሜሪካ እንግዳ የሆነ ድርጊት ተከትሎ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤዋ ናንሲ ፔሎሲ 25ኛውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በመጥቀስ ትራምፕ አሜሪካንን ለመምራት ብቁ ስላልሆኑ ከዋይት ሐውስ እንዲባረሩ ጥያቄ አቅርበዋል።
ይህን ጥያቄ በርካታ ዲሞክራቶችና ጥቂት ሪፐብሊካኖች ጭምር ድጋፍ ሰጥተውታል። የሴኔት ዲሞክራት ተጠሪ ቸክ ሹመር ትራምፕ አመጽ በማቀጣጠላቸው ከሥራ ሊባረሩ ይገባል ብለዋል።
ቸክ ሹመር አክለውም "ምክትል ፕሬዝዳንቱ እና ካቢኔው ይህንን ለማድረግ የማይፈልጉ ከሆነ፣ ኮንግረሱ ዳግመኛ ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን እንዲነሱ ለማየት መሰብሰብ አለበት" ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሐውስ እንዲወገዱ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን ለድርጊታቸው ክስ እንዲመሰረትባቸውም ናንሲ ፒሎሲ ጥሪ አድርገዋል።
ክሱ ተፈጻሚ እንዲሆን ግን ዲሞክራቶች የሪፐብሊካኖችን ድጋፍ ማግኘት አለባቸው። ምክንያቱም ክሱ እንዲፈጸም የምክር ቤቱ ሁለት ሦስተኛው ድምጽ ስለሚያስፈልግ ነው። ይህ የመሳካት እድሉም አነስተኛ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ይህ እንዴት ሊሰራ ይችላል?
25ኛው አሜንድመንት ፕሬዝዳንቱ ኃላፊነቶቹን መወጣት በማይችልበት ጊዜ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ስልጣኑን በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት ተረክቦ እንዲያስተዳድር ይፈቅዳል።
ለምሳሌ ፕሬዝዳንቱ በአእምሮም ሆነ በአካላዊ ጤና ምክንያት ኃላፊነታቸውን መወጣት ባይችሉ እንደማለት ነው።
በአሁኑ ሰዓት መነጋገሪያ እየሆነ ያለው የዚህ አሜንድመት አንቀጽ አራት ነው። ይህ አንቀጽ ምክትል ፕሬዝዳንቱ እንዲሁም የካቢኔው አብላጫ አባላት ፕሬዝዳንቱ ኃላፊነታቸውን መወጣት አልቻሉም ብለው እንዲወስኑ እድል ይሰጣቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፊርማቸው ያረፈበትን ደብዳቤ መላክ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ሴኔቱም ፕሬዝዳንቱ ሥልጣንና ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ብቁ አይደሉም ሲል ያፀድቃል።
በዚህ ጊዜ ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ሙሉ በሙሉ ሥልጣኑን ተረክበው አገሪቱን ማስተዳደር ይጀምራሉ።
ፕሬዝዳንቱ በጽሁፍ ምላሽ እንዲሰጡ እድል የሚሰጣቸው ሲሆን ውሳኔውን ተቃርነው ከቀረቡ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ እንዲወስን ይደረጋል።
ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣናቸው ለማውረድ በታህታይና ላዕላይ ምክር ቤት አባላት የሚሰጥ የትኛውም ድምጽ አብላጫውን ወይንም ሁለት ሦስተኛውን ማግኘት አለበት።
ይህ ጉዳይ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስም ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን ተረክበው ያስተዳድራሉ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ 25ኛው አሜንድመንትን ለመጠቀም ንግግር ሲደረግ ይህ መጀመሪያው አይደለም።
ፕሬዝዳንቱ በኮቪድ-19 ተይዘው በነበረበት በጥቅምት ወር ላይ አገሪቱን ለመምራት ሕመማቸው አያስችላቸውም በሚል ተነስቶ ነበር።
በዚሁ ወቅት የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ናንሲ ፔሎሲ፣ በ25ኛው አሜንድመንት ላይ መሰረት ያደረገ እና የፕሬዝዳንቱን ጤና ለሥራ ብቁ መሆን አለመሆኑን የሚፈትሽ ሕግ አስተዋውቀው ነበር።
ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ውሎ ያውቃል?
25ኛው አሜንድመንት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1967፣ ጆን ኦፍ ኬኔዲ ከተገደሉ አራት ዓመት በኋላ፣ ፕሬዝዳንቱ በተለያየ ምክንያት ሥልጣንና ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ ወቅት ማን ይተካቸዋል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በሚል ጸድቋል።
በዚህም የተነሳ በርካታ ፕሬዝዳንቶች ይህንን የሕግ ማሻሻያ [አሜንድመንት]፣ በይበልጥ ደግሞ በጊዜያዊነት ሥልጣንን ለምክትላቸው ማስተላለፍ የሚፈቅደውን ክፍል፣ አንቀጽ ሦስትን ተጠቅመውበታል።
በ2002 እና በ2007 ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ የአንጀት ህክምና በሚያደርጉበት ወቅት ምክትላቸው እንዲተኳቸው አድርገዋል። ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን በ1985 ለካንሰር ህክምና ሆስፒታል በገቡበት ወቅት ተመሳሳዩን አድርገዋል።
ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ 25ኛው አሜንድመንትን በመጠቀም የትኛውም ፕሬዝዳንት ከሥልጣን እንዲወርድ ተደርጎ አያውቅም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን በሌላ በምን ምክንያት ሊወርዱ ይችላሉ?
ዲሞክራቶች ፕሬዝዳንት ትራምፕ የፖለቲካ ተቀናቃኛቸውን ለማጥፋት ከውጪ ኃይሎች ድጋፍ ጠይቀዋል በሚለው ውንጀላ የተነሳ እንዲጠየቁላቸው ክስ አቅርበው ነበር።
በወቅቱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ውንጀላውን የካዱ ሲሆን " የሌለን ነገር ፍለጋና እርባና ቢስ" ሲሉ አጣጥለውታል።
ውንጀላው የተሰማው ፕሬዝዳንቱ ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር ያደረጉትን የስልክ ልውውጥ ተከትሎ በቀረበ መረጃ ላይ ነው።
መረጃውን ለዲሞክራቶች ሹክ ያለው ግለሰብ ማንነት ባይገለጽም፣ ትራምፕ ዩክሬን የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና ልጃቸው ላይ የሙስና ምርመራ እንድትጀመር በወታደራዊ እርዳታ አስታከው አስፈራርተዋል ብለዋል ዲሞክራቶች።
ይህም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታሪክ በሥልጣን ላይ እያሉ የተከሰሱ ብቸኛው ፕሬዝዳንት ያደርጋቸዋል።
የአሜሪካ ሕገመንግሥት ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን ሊወርድ የሚችልባቸውን ምክንያቶች ሲዘረዝር "በአገር መክዳት ወንጀል፣ ሙስና አልያም በሌላ ከፍተኛ ወንጀል ወይንም በደል ፈጽመው ከተከሰሱ" ነው ይላል።
ይህ ግን ከወንጀል ይልቅ ፖለቲካዊ ነው።
እንዲህ አይነት ጉዳዮች ሁለት ደረጃዎች ያሏቸው ሲሆን በመጀመሪያ ለተወካዮች ምክር ቤት ይቀርብና ካለፈ ወደ ሴኔቱ ተመርቶ ይታያል።
ነገር ግን በአሜሪካ ታሪክ ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን ለማውረድ የሚያበቃ አብላጫ ሁለት ሦስተኛ የተወካዮች ድምጽ ተገኘቶ አያውቅም።
















