የአሜሪካ ምክር ቤት፡ የጆ ባይደንን የምርጫ ውጤት አረጋገጠ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ምክር ቤቶች የጆባይደንን የምርጫ ውጤት አረጋገጡ።
የሁለቱ ምክር ቤት እንደራሴዎች የተሰጡትን የውክልና ድምጾች (ኤሌክቶራል ቮት) በመቁጠር ጆ ባይደን ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን አረጋግጧል።
ኮንግረስ ጆባይደን እና ምክትላቸው ካምላ ሀሪስን ቀጣዮቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት በማድረግ ያገኙትን ድምጽ አጽድቋል።
የተሰጡት የውክልና ድምጾች የጸደቁት የሁለቱ ምክር ቤት ተወካዮች በፔንሰልቫንያ እና አሪዞና ግዛቶች የቀረበውን ተቃውሞ ውድቅ ካደረጉ በኋላ ነው።
የአገሪቱ ሕዝብ እንደራሴዎች ተሰብስበው ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የምርጫ ውጤት ዙሪያ በመነጋገር ላይ ሳሉ በድንገት በሺህ የሚቆጠሩ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ምክር ቤቱን ሰብረው ገብተዋል።
በዚህም የተነሳ ተቋርጦ የነበረው የምክር ቤቶቹ የጋራ ስብሰባ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ቀጥሏል።
ዋሺንግተን ውስጥ የተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች የአገሪቱን ምክር ቤት ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ በተፈጠረ ፍጥጫ አራት ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
በተቀሰቀሰው ግርግር ሳቢያ የዋሺንግተን ከንቲባ በከተማዋ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥለዋል። የካፒቶል ሂል አካባቢም ሙሉ በሙሉ ዝግ እንዲሆን ተደርጓል።
ከጥቃቱ በኋላ ጆ ባይደን በቴሌቪዥን ቀርበው በቀጥታ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር"በአሜሪካ ዲሞክራሲ ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል" ብለዋል። ተቀናቃኛቸው ትራምፕም በአስቸኳይ ወጥተው ውንብድና ላይ ያሉ ደጋፊዎቻቸውን አደብ እንዲያሲዙ ጠይቀዋል።
ካፒቶል ሒል በነውጥ ላይ እያለ ከዋሺንግተን ዲሲ በሚጎራበቱ ግዛቶች የአሜሪካ ወታደሮች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ሆነዋል። የካፒቶል ሒል ፖሊሶችን ለመደገፍም ኤፍቢአይ ወደ ስፍራው ተሰማርቷል።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ማን ናቸው?
ጆ ባይደን ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት በመሆን ተመርጠዋል።
ባይደን የባራክ ኦባማ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል።
ደጋፊዎቻቸው ባይደን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አዋቂ ናቸው ይሏቸዋል። በእርጋታቸው የሚታወቁት ፖለቲከኛ በግል ሕይወታቸው አሳዛኝ ክስተቶችን አሳልፈዋል።
ባይደን የፖለቲካ ሕይወታቸው የጀመረው ከ47 ዓመታት በፊት ነበር። የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን ጥረት ማድረግ የጀመሩት ደግሞ ከ33 ዓመታት በፊት እአአ 1987 ላይ።
ባይደን በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት አላቸው።
የቀረቡባቸው ክሶች
ከአንድ ዓመት በፊት 8 ሴቶች ባይደን ጾታዊ ትንኮሳ አድርሰውብናል በማለት አደባባይ ወጥተው ነበር። እነዚህ ሴቶች ባይደን ባልተገባ መልኩ ነካክቶናል፣ አቅፎናል አልያም ስሞናል የሚሉ ክሶችን ይዘው ነው የቀረቡት።
ይህንን ተከትሎ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ባይደን ከዚህ ቀደም በይፋዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ሴቶችን በጣም ተጠግተው ሰላምታ ሲሰጡ የሚያሳዩ ምስሎችን አውጥተው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአንዳንድ ምስሎች ላይ ደግሞ ባይደን ሴቶችን በጣም ተጠግተው ጸጉር የሚያሸቱ የሚመስሉ ምስሎችን አሳይተዋል።
ከወራት በፊትም ረዳታቸው የነበረች ታራ ሬዲ የተባለች ሴት ባይደን ከ30 ዓመታት በፊት ከግደግዳ አጣብቀው ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽመውብኛል ብላ ነበር።
ባይደን በበኩላቸው "ይህ በፍጹም አልተከሰተም" በሚል አስተባብለዋል።
ስህተቶችን ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት
ባይደን በዋሽንግተን ፖለቲካ ውስጥ ረዥም ልምድ አላቸው። 8 ዓመታትን በተወካዮች ምክር ቤት፣ 8 ዓመት ሴናተር በመሆን፣ 8 ዓመት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት በመሆን አገልግለዋል።
ይህ ግን ፕሬዝደንታዊ ምርጫን ለማሸነፍ ሁሌም በቂ አይሆንም።
28 ዓመታትን በሴኔት ውስጥ ያሳለፉት ጆና ኬሪ እንዲሁም 8 ዓመታትን በሴኔት እንዲሁም 8 ዓመታት ቀዳማዊት እመቤት ሆነው ያገለገሉት ሂላሪ ክሊንተር ከነሱ ያነሰ የፖለቲካ ልምድ ባላቸው እጩዎች ተሸንፈዋል።
የባይደን ደጋፊዎች ግን ባይደን ይህ እጣ እንደማይገጥማቸው ተስፋ አድርገዋል።
ረዥም ታሪክ
ባይደን ባለፉት አስርት ዓመታት በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ በተላለፉ ቁልፍ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ውስጥ ተሳትፎ አላቸው ወይም ተሳትፎ እንዳላቸው ይነገራል።
ይህ ታዲያ አሜሪካ አሁን ባለችበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ በጥሩ መልኩ የሚታይ አይደለም።
ለምሳሌ እአአ በ1970ዎቹ በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ጥቁር እና ነጭ ተማሪዎችን ለማሰባጠር ተማሪዎች ከሚኖሩባቸው ቦታዎች በአውቶብስ በሟጓጓዝ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለመመደብ የተደረገውን ጥረት ተቃውመው ነበር።
በዚህም ዘንድሮ ባካሄዱት የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሲተቹ ቆይተዋል።
እአአ 1991 ላይ የባህረ ሰላጤውን ጦርነት ተቃውመው እአአ 2003 ላይ አሜሪካ ኢራቅን እንደትወር ደግፈዋል። መልሰው ደግሞ ባይደን አሜሪካ ወደ ኢራቅ መሄዷ ትክክል አልነበረም በማለት ትችት ሲሰነዝሩ ተሰምተዋል።
ባይደን ባለቤታቸውን እና ሴት ልጃቸውን በመኪና አደጋ ምክንያት በሞት ተነጥቀዋል።
ባይደን የመጀመሪያ የሴኔት ድላቸውን ተከትሎ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ባለቤታቸው የመኪና አደጋ አጋጥሟቸው ነበር። ባለቤታቸው እና ሴት ልጃቸው ሕይወታቸው ሲልፍ ሃንተር እና ቤኡ የተባሉት ሁለት ወንድ ልጆቻቸው ላይ ጉዳት ደርሷል።
ቤኡ እአአ 2015 ላይ በአእምሮ ኢጢ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። በሕይወት ያለው ቀሪው ልጃቸው ሃንተር ጠበቃ ሆነ። ገንዘብ ግን ሕይወቱን ከቁጥጥር ውጪ አደረገበት።
ከዚያም ሃንተር ከባለቤቱ ጋር ተፋታ። በፍቺው ወረቀት ላይ የሃንተር የቀድሞ ባለቤት ሃንተር አልኮል እና አደንዛዥ እጽ እንደሚጠቀም እንዲሁም የምሽት መዝናኛ ክበቦችን እንደሚያዘወተር ገልጻለች።
ሃንተር በተደረገለት ምርመራ ኮኬይን በሰውነቱ ውስጥ በመገኘቱ ከአሜሪካ ጦር ባህር ኃይል ተጠባባቂነት ተሰርዟል።
ከዛም ሃንተር ባለፈው ዓመት አንድ ሳምንት ብቻ ካወቃት ሴት ጋር ትዳር መስርቷል። ይህም የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካምላ ሃሪስ ማን ናቸው?
ካምላ ሃሪስ የመጀመሪያዋ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ታሪክ ሰርተዋል።
ይህም ብቻ የመጀመሪያዋ ጥቁር እና እስያ አሜሪካዊ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን በታሪክ መዝገብ ላይ ይሰፍራሉ።
ካማላ ሕንዳዊ ከሆኑት እናታቸው እና ጃማይካዊ ከሆኑት አባታቸው በካሊፎርኒያ ነበር የተወለዱት።
የ55 ዓመቷ የካሊፎርኒያ ሴናተር በዚህ ወሳኝ ወቅት ከተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጋር በመሆን አሜሪካንን ለቀጣይ አራት ዓመታት ይመራሉ።
ካማላ ገና በልጅነታቸው ወላጆቿ መፋታታቸውን ተከትሎ እናታቸው ነበሩ ያሳደገቿው።
የካማላ እናት እውቅ የካንስር ሕመም ተመራማሪ እና የመብት ተሟጋች ነበሩ።
ካማላ አስተዳደጋቸው የህንድ ባህል የተከተለ ነበር። ከወላጅ እናታቸው ጋር በተደጋጋሚ ለጉብኝት ወደ ህንድ ይጓዙ ነበር። ይሁን እንጂ ካማላ ወደ ፖለቲካው ከገቡ በኋላ ወላጅ እናታቸው ያሳደጓቸው የጥቁር አሜሪካውያንን ባህል እና አኗኗርን በተከተለ መልኩ ነበር።
"እናቴ ሁለት ጥቁር አሜሪካውያንን እያሳደገች እንደሆነ ነው የምትረዳው። ያደግነበት ማህብረስብ እኔን እና እህቴን እንደ ጥቁር ሴቶች አድርጎ እንደሚቀበለን ተረድታ ነበር" በማለት ካማላ የሕይወት ታሪካቸውን በያዘው መጽሐፍ ላይ አስፍረዋል።
ካማላ በልጅነት እድሜያቸው በካናዳ ኖረዋል። ወላጅ እናታቸው ካናዳ በሚገኘው ማክጊል ዩኒቨርሲቲ መምህር ነበሩ። በካናዳዋ ሞንትሪያል ለአምስት ዓመታት ኖረዋል።
የኮሌጅ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ደግሞ በአሜሪካዋ ሆዋርድ ዩኒቨርሲቲ ነው። ከአራት ዓመታት የትምህርት ቆይታ በኋላ ካማላ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ለመስራት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያን ተቀላቅለዋል።
ካማላ ዐቃቤ ሕግ በመሆን ረዘም ላለ ዓመታት አገልግለዋል። እአአ 2003 ላይ ካማላ የመጀመሪያዋ የካሊፎርኒያ ጥቁር ሴት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመሆን ተመርጠዋል።
እአአ 2014 ላይ የሕግ ባለሙያ ከሆኑት ዶግ ኤምሆፍ ጋር ትዳር መስረተዋል።












