ካፒቶል ሒልን ጥሰው የገቡ አመጸኞችን ለመያዝ የኤፍቢአይ አደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ በካፒቶል ሒል ሕንጻ ላይ የትራምፕ ደጋፊዎች የተቃውሞ ግርግር ከፈጠሩ በኋላ ኤፍቢአይ አመጸኞቹን ለፍርድ ለማቅረብ ሕዝቡ እንዲጠቁመው ጠይቋል።
ነውጠኞቹ ባለፈው ረቡዕ የትራምፕ ደጋፊዎች በካፒቶል ሒል ሕንጻ ተሰብስበው ጥሰው በመግባት የጆ ባይደንን የምርጫ አሸናፊነት በመቃወም የሕዝብ እንደራሴዎችን ስብሰባ አወከዋል።
በዚህም በሕንጻው ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የአፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ረዳትም ላፕቶፓቸው መሰረቁ ታውቋል።
ከአመጸኞቹ መካከል የ60 ዓመቱ ሪቻርድ ባርኔት ወደ ካፒቶል ሒል ሕንጻ ከገቡት ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆን አሁን በፖሊስ ተይዞ እስር ላይ ነው። ባርኔትን ለመለየትና ለመያዝ አስቸጋሪ ስላልነበረ ነው በቀላሉ የተያዘው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ባርኔት በግርግሩ ውስጥ ወደ ካፒቶል ሒል ገብቶ በአፈ ጉባኤዋ ናንሲ ፔሎሲ ቢሮ ውስጥ እግሩን ጠረጴዛ ላይ ሰቅሎ የተነሳው ፎቶግራፍ ወዲያውኑ ነበር በዓለም ዙሪያ በስፋት ተሰራጭቷል። ግለሰቡ ከሌሎች ጋር በመተባበር የሕዝብን ንብረት በመዝረፍ ክስ ተመስርቶበታል።
የምዕራብ ቨርጂኒያ ሕግ አውጭ አባል የሆኑት ዴሪክ ኢቫንስም በተቃውሞው ወቅት በቦታው ተገኝተው ከተቃዋሚዎች ጋር በመሆን የቀረጹትን ቪዲዮ በኦንላየን በማጋራታቸው ክስ ተመስርቶባቸዋል።
የፌደራል የሕግ አስፈጻሚ አካላት እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎች ረቡዕ ላይ በነበረው ግርግርና ጥፋት ምክንያት ክስ ተመስርቶባቸዋል። በሚቀጥሉት ቀናት ተጨማሪ በዛ ያሉ እስራቶች ይኖራሉ ተብሎም ይጠበቃል።
እስካሁን በተካሄደው ምርመራ የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም የሕዝቡ ጥቆማ አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይም ተቀጣጣይና ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን ይዞ አመጽ በማነሳሳት ወንጀል ከከባድ እስከ ቀላል ክስ ይመሰረትባቸዋል ተብሏል።
ምናልባትም በእዚሁ ክስ በርካታ ዓመታትን በእስራት እንዲቆዩ የሚያደርግ ቅጣት ሊበየንባቸው እንደሚችል ይጠበቃል። በአሁኑ ጊዜ የኤፍቢአይ መርማሪዎች የተጠርጣሪዎችን ፎቶ ይዘው ሰዎች እንዲጠቁሟቸው እየጠየቁ ነው።
ይህንን መነሻ በማድረግም ረቡዕ ዕለት በካፒቶል ሕንጻ የተሳተፉ ሰዎችን ለማደን እየሠሩ ነው። አደኑ ደግሞ በመላው ከተማ [ዋሽንግተን ዲሲ] እና አለፍ ሲልም በመላዋ አሜሪካ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
እስካሁን ያሉት እውነታዎች ምንድን ናቸው?
- አንድ የካፒቶል ሒል የፖሊስ አባልን ጨምሮ አምስት ሰዎች ሞተዋል
- እስካሁን ቢያንስ 82 ሰዎች ታስረዋል
- እስካሁን መርማሪዎች በዋሽንግተን ዲሲ ብቻ 17 ሺህ መረጃዎችን ከሕዝብ ሰብስበዋል።
- በሪፐብሊካን እና ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ዋና ጽህፈት ቤቶች ላይ ቦምብ ያጠመዱ ሰዎችን ለሚጠቁም ኤፍቢአይ የ50 ሺህ ዶላር ሽልማት እንደሚሰጥ አሳውቋል።
ያም ሆኖ ግን ከሕዝቡ የሚመጡ ጥቆማዎችን ለመለየት ተጨማሪ ሥራዎች ያስፈልጋሉ። ምናልባት አንዳንድ ጊዜ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ከዜጎች የሚመጡ መረጃዎች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ሊያመዝን ይችላል ተብሏል።
በ2013 (እአአ) የቦስተን ቦምብ ፍንዳታ ከተከሰተ በኋላ ከቦስተን ማራቶን አቅራቢያ ላይ የተነሳ ሁለት የጉዞ ሻንጣ የያዙ እና የሚያወሩ ሰዎች ምስል በኦንላይን ይዘዋወር ነበር። እናም ሌላው ሰው እነዚህን ሰዎች "ወንጀለኞቹ ናቸው" ይላቸው ነበር።
እውነታው ግን እነዚህ ሰዎች ከጥቃቱ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም። በተመሳሳይም የካፒቶል ሒል ግርግር ተሳታፊዎችንም በትክክል ያልጠቆመ መረጃ ሊሰጥ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ለምሳሌ አንዳንድ የትራምፕ ደጋፊዎች አመጹን ከአንቲፋ ወይም ከብላክ ላይቭስ ማተር ጋር ሲያገናኙት ነበር፤ ነገር ግን ይህንን የሚያረጋግጥ መረጃ ግን እስካሁን አልተገኘም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ አሜሪካውያን ይህን አመጽ የቀሰቀሱ ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ይፈልጋሉ። በአሜሪካ ፍትህ ሚንስቴር ውስጥ የወንጀል ዘርፍ ጋር የሚሰሩት የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰሩ ስቴፈን ሳልዝበርግ፣ ሕብረተሰቡ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ለመጠቆምና ኤፍቢአይን ለመተባበር ከፍተኛ መነሳሳት እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
"ሰዎች ስለዲሞክራሲ ይጨነቃሉ፣ አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት አግኝተው ማየት ይፈልጋሉ፣ ፍትህ ሰፍኖ ማየት ይሻሉ" ብለዋል።















