አሜሪካ ፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ ክስ እንዲከፈት ግፊት እየተደረገ ነው

ዶናልድ ትራምፕ፡ ዴሞክራቶች ፕሬዝዳንቱን ለመክሰስ የሚረዳቸው አንቀፅ ለማስተዋወቅ አቅደዋል

አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ

ዲሞክራቶች ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ካፒቶል ሒል እንዲወረር በነበራቸው ሚና ምክንያት እንዲከሰሱ የሚያደርግ አንቀፅ ለማስተዋወቅ አቅደዋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስልጣናቸውን በፍጥነት ካልለቀቁ በጉዳዩ እንደሚገፉ ገልጸዋል።

በፕሬዝዳንቱ ላይ "የአመጽ ማነሳሳት" ክስ ዴሞክራቶች ሰኞ ዕለት ይከፈታልም ተብሎ ይጠበቃል።

በኮንግረሱ ውስጥ አምስት ሰዎች የሞቱበትን አመፅ በማበረታታት ትራምፕን እጃቸው አለበት በሚል ይከሳሉ።

የተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትራምፕን ከስልጣን የማነሳቱ ጉዳይ የኮንግረስ ውሳኔ እንደሆነ ቢናገሩም "ለረዥም ጊዜ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሥራውን ለመያዝ ብቁ አይደሉም" ብለው ሲያስቡ እንደነበር ተናግረዋል።

ዋይት ሐውስ በበኩሉ ክሱን "ታላቋን አገራችንን የበለጠ ለመለያየት ብቻ የሚያገለግል፤ በፖለቲካዊ ፍላጎት የተሞላ" እርምጃ ነው ሲል አጣጥሎታል።

ወደ 160 የሚጠጉ የምክር ቤቱ ዴሞክራቶች ረቂቁን የፈረሙ ሲሆን፣ የካሊፎርኒያው ቴድ ሊዩ እና የሮድ አይላንዱ ዴቪድ ሲሲሊ ረቂቁን ማዘጋጀት ጀምረዋል።

ሂደቱ ከቀጠለ ምክር ቤቱ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ የከስልጣን የማንሳት ክስን ሲያቀርብ ለሁለተኛ ጊዜው ይሆናል።

ባለፈው ዓመት በታችኛው ምክር ቤት ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀማቸው እና የኮንግረሱን ሥራ በማደናቀፍ ክስ ትራምፕን ከስልጣን ለማንሳት ክስ ቀርቦባቸው ነበረ። ነገር ግን ሴኔቱ በየካቲት 2020 በሁለቱም ክሶች ነጻ እንዳደረጋቸው ይታወሳል።

ከዚህ በፊት አንድም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሁለት ጊዜ ክስ ከሥልጣን የሚያስነሳ አልተመሰረተበትም። በሴኔት ውስጥ የትራምፕ ፓርቲ የሆነው ሪፐብሊካን ሰፊ ድጋፍ ስላለው ጉዳዩ የሚሳካ አይመስልም።

የሪፐብሊካን ሴናተር የሆኑት የአላስካዋ ሊዛ ሙርኮቭስኪ አርብ ለአንኮራጅ ዴይሊ ኒውስ እንደተናገሩት ትራምፕ "ስልጣን መልቅቅ አለባቸው" ብለዋል። ትራምፕን በመተቸት የሚታወቁት የኔብራስካው የሪፐብሊካኑ ሴናተር ቤን ሳሴ በበኩላቸው ክሱን ሊደግፉት እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ነገር ግን የፕሬዚዳንቱ ፓርቲ አባላት ትራምፕን ለመክሰስ ስለመስማማታቸው እስካሁን ድረስ ፍንጭ የለም።

ይህም የምክር ቤቱ ክስ ትራምፕን ለኮንግረሱ ወረራ ተጠያቂ ለማድረግ የሚጠቅም እርምጃ ብቻ ሊሆን ይችላል።

አንድ የሴኔት ማስታወሻ እንደሚገልጸው ምክር ቤቱ ማንኛውንም ክስ ሊቀበል የሚችለው ትራምፕ የስልጣን ዘመናቸው ከማለቁ ከአንድ ቀን በፊት እንደሚሆን ሲገልጽ ይህም የፍርድ ሂደቱ ሊጀመር የሚችለው ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ብቻ እንደሆነ ያስታውቃል።

የሕገ-መንግሥት ባለሙያዎች በዚህ ክስተት ውስጥም ቢሆን ክሱ ወደ ሴኔት መሻገር መቻሉ ላይ ተከፋፍለዋል።

ትራምፕ ጥፋተኛ ከተባሉ ለቀድሞ ፕሬዚዳንቶች የሚሰጣቸውን ጥቅማ ጥቅምን የሚያጡ ሲሆን፤ ሴናተሮች በቋሚነት ከመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች እንዲታገምዱ ድምጽ መስጠት ይችላሉ።

የካፒቶል ሒል ወረራ ከፍተኛ ፖለቲከኞችን በእጅጉ ያሳሰባቸው ሲሆን፣ አፈ-ጉባኤ ፔሎሲም ትራምፕ የኒውክሌር ኮዶችን እንዳያገኙ ለመከላከል ስለሚቻልባቸው መንገዶች ከአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ጋር እንዲነጋገሩ አስገድዷቸዋል።

ረቂቁ ምን ይላል?

የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ያገኘው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ "አመጽ ማነሳሳት" የሚል ሃሳብ የያዘ ነው።

ረቂቁ "ዶናልድ ጆን ትራምፕ ሆን ብለው በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ላይ ሁከትን በማነሳሳት በከፍተኛ ወንጀልና በደል ላይ ተሰማርተዋል" ይላል።

ፕሬዚዳንቱ "በካፒቶል ሒል ላይ ሕገወጥ እርምጃን የሚያበረታቱ መግለጫዎችን በመናገራቸውም" ይከሳሉ።

ረቂቁ በተጨማሪም ይህ ድርጊታቸው በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተመረጡት ባይደን ያሸነፉበትን የምስክር ወረቀት "ለማደብዘዝ እና ለማደናቀፍ ከቀድሞ ጥረቶቹ ጋር የሚጣጣም ነበር" ብለዋል።

"በአሜሪካ ሕዝብ ላይ በግልጽ የሚታይ ጉዳት አድርሷል" ተብሏል።

ባይደን በምርጫው የውክልና ድምጽ ባገኙት ውጤት አሸናፊነታቸው በኮንግረስ በተረጋገጠበት ቀን ፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎቻቸው ወደ ካፒቶል ሒል እንዲሄዱና አበረታተዋል ተብለው እተወቀሱ ነው።

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ትክክለኛነትን ጥርጣሬ ውስጥ የከተተ የድጋፍ ሰልፍ ከማካሄድ ባለፈ ያለማስረጃም "ምርጫው የተጭበረበረ" መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ወደ ካፒቶል አቅንተን ደፋር ሴናተሮቻችንን እና የኮንግሬስ አባላቶቻችንን እናበረታታለን" ሲሉ የተናገሩት ትራምፕ ደጋፊዎቻቸውን "እንዲታገሉ" አሳስበዋል።

ዴሞክራቶች እና አንዳንድ ሪፐብሊካኖች እነዚህ ቃላት ከማነሳሳት ጋር የተቆራኙ ናቸው ሲሉ ተከራክረዋል።

በአሜሪካ መንግሥት ሕጎችን አርቅቆ ሚያወጣው ኮንግረስ ፕሬዚዳንቶችን ለፍርድ ለማቅረብ ይችላል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፕሬዚዳንቱ ላይ ክሶች ማቅረብ ይችላሉ። ምክር ቤቱ ክሱን ለማሳለፍ ድምጽ ከሰጠ ፕሬዝዳንቱ ጥፋተኛ መሆን አለመሆናቸውን ወደ የሚወስነው ወደ ሴኔት ይመራል።

ይህም ከወንጀል ይልቅ ያልተለመደ ክስተት እና የፖለቲካ ሂደት ነው።

ትራምፕ ተመሳሳይ ክስ ሲቀርብባቸው ሦስተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ናቸው።

ሁለቱ በጎርጎሮሳዊያኑ 1999 ቢል ክሊንተን እና አንድሪው ጆንሰን ደግሞ በ1868 ናቸው።

ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ከመከሰሳቸው በፊት ስልጣናቸውን ለቀዋል።

እንዴት እዚህ ደረስን?

ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው ዲሞክራቶች ጥረቱን በከፍተኛ ደረጃ ይደግፉ የነበረ ሲሆን የኦሪገኑ ተወካይ ከርት ሽራደር ብቻ እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ አገሪቱን ይበልጥ የሚከፋፍል ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

ፔሎሲ የመረጡት ሃሳብ ትራምፕ በ 25ኛው አሜንድመነት መሠረት በአእምሮ ወይም በአካላዊ ህመም ሳቢያ ተግባራቸውን ማከናወን ካልቻሉ ምክትል ፕሬዚዳንቱ እንዲተኩ የሚያደርገው ሕግ እንዲተገበር እየጠየቁ ነው።

ይህ ካልሆነ ግን ፕሬዝዳንቱን በመክሰስ ከስልጣን ማወረድ ሌላኛው ሃሳብ ነው።

ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ በጣም የማይታሰብ ነው ተብሏል። ምክትል ፕሬዝዳንት ፔንስም አሜንድመንቱን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን የሚያሳይ ምልክት የለም።

ፔሎሲ አርብ ዕለት ኮንግረሱ ትራምፕ በስልጣን ላይ እያሉ አሜሪካውያንን ለመጠበቅ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።