ፕሬዚዳንት ትራምፕ የካፒቶሉን ነውጥ በማነሳሳት እንዲከሰሱ ተወሰነ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ህግ መምሪያ ምክር ቤት እንደራሴዎች ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን የካፒቶሉን ነውጥ አነሳስተዋል በሚል እንዲከሰሱ ውሳኔ አስተላልፈዋል።

ከስልጣን ሊለቁ ቀናት የቀራቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲገፈፍና በአመፅና ሁከት እንዲከሰሱም ለማስቻል እንደራሴዎቹ በአብላጫ ድምፅ ነው የወሰኑት።

የፕሬዚዳንቱ ፓርቲ አባል የሆኑ አስር ሪፐብሊካኖችም ከዲሞክራቶቹ ጋር በመወገን 232 በ197 ድምፅ ብልጫ አግኝቶ ክሱ አልፏል።

በስልጣን ላይ እያሉ ሁለት ጊዜ እንዲከሰሱ የተወሰነባቸው ወይም ኮንግረሱ በወንጀሎች የጠየቃቸው የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት አድርጓቸዋል።

ሪፐብሊካኑ ትራምፕ በባለፈው የተደረገውን ምርጫ ውጤት ለመቀልበስ ደጋፊዎቻቸውን ለአመፅ አነሳስተዋል በሚልም በምክር ቤቱ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙም እስከ ወዲያኛው ድረስ መቼም ቢሆን በስልጣን ቦታ ላይ እንዳይቀመጡ ይደረጋል።

ነገር ግን ስድስት ቀናት በቀረው የስልጣን ሽግግር ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከስልጣን መወገድም ሆነ መልቀቅ አይጠበቅም።

ለዚህም ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ ምክር ቤቱ ጉባኤውን በተባለው ወቅት ላያካሂድ ይችላል።

ጥቅምት 24 በተደረገው ምርጫ በዲሞክራቱ ጆ ባይደን የተሸነፉት ትራምፕ ስልጣናቸውን ጥር 11/ 2013 ዓ.ም ያስረክባሉ።

ፕሬዚዳንቱ የምርጫውን ውጤት በፀጋ መቀበል አለመቻላቸው በከፍተኛ ሁኔታም ውግዘት አትርፎላቸዋል።

በትናንትናው ዕለት በባለፈው ሳምንት ሁከት በተቀሰቀበት ካፒቶል ሂል የትራምፕን ክስ አስመልክቶ የህግ መምሪያ ምክር ቤት እንደራሴዎቹ በትናንትናው ዕለት ረዥም ሰዓታት የፈጀ ክርክርም አድርገዋል።

በህንፃው ውስጥና ውጭም የብሄራዊ ዘብ በከፍተኛ ትጥቅም የፀጥታውን ደህንነት ሲጠባበቅም ነበር ተብሏል።

በምክር ቤቱ የተካሄደውን የድምፅ አሰጣጥ ሁኔታም ተከትሎ ትራምፕ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ደጋፊዎቻቸው ሰላማዊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በመልዕክታቸው ስለ ክሱ ምንም ነገር ያላሉት ትራምፕ "ሁከትና ጥፋት በአገራችን ቦታ የላትም። የኔ እውነተኛ ደጋፊዎች በምንም መንገድ ፖለቲካዊ ሁከትን አይቀበሉም" በማለትም እርቅ ያዘለ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከዚሁም ጋር በተያያዘ ትራምፕን የሚደግፉ ነውጦች በመላው አሜሪካ ግዛቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ የአሜሪካው የፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ ከቀናት በፊት አስጠንቅቋል።

መጪው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ሹመታቸውን ከሚረከቡበት ቀንም ቀድመው ሊከሰቱ እንደሚችሉ ቢሮው መረጃ ደርሶኛል ብሏል።

በጦር መሳሪያ የታገዙ ሁከቶች ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ በአምሳ የተለያዩ ግዛቶች መታቀዳቸውን ሪፖርቶች ቢሮው አግኝቷል።

ጆ ባይደን ከስምንት ቀናት በኋላ በዓለ ሲመታቸው የሚካሄድ ሲሆን የዝግጅቱንም የፀጥታ ሁኔታ ለማስጠበቅ ከፍተኛ የደህንነት ስራዎች እየተሰራ ቢሆንም ፍራቻዎች ነግሰዋል።