አሜሪካዊው ራፐርና ፕሮዲዩሰር ዶ/ር ድሬ ሆስፒታል ገባ

አሜሪካዊው ራፐርና ፕሮዲውሰር ዶ/ር ድሬ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ ስኬታማ እና ተደማጭነት ካላቸው አሜሪካውያን መካከል አንዱ የሆነው ራፐር እና ፕሮዲዩሰር ዶ/ር ድሬ በአንጎል የደም ቧንቧ ችግር ምክንያት በሆስፒታል ህክምና እየተደረገለት ይገኛል፡፡

የ55 ዓመቱ ዶ/ር ድሬ ሎስ አንጀለስ ወደ ሚገኘው ሴዳርስ-ሲናይ ህክምና ማዕከል ተወስዷል ሲል ቲኤምዚ ዘግቧል፡፡

ዶ/ር ድሬም በኢንስታግራም ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ ላይ "ጥሩ እያገገምኩ እና በህክምና ቡድኔ ጥሩ እንክብካቤ እያገኘሁ ነው" ብሏል፡፡

ከበሽታው በኋላ "እረፍት እያደረገ ነው" ሲሉ ጠበቃው ለቢልቦርድ ተናግረዋል፡፡

"ከሆስፒታል ወጥቼ በቅርቡ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ፡፡ በሴዳር ለሚገኙ ታላላቅ የህክምና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርቡልኝ፡፡ አንድ ፍቅር" ሲል ዶ/ር ድሬ ያለበትን አካፍሏል።

የጤንነቱ ሁኔታ ከተገለጸ በኋላ ጓደኞቹ እና ባልደረቦቹ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሥራ ባልደረባው አይስ ኪዩብ በትዊተር ገፁ ላይ "ፍቅራችሁን እና ጸሎታችሁን ለዶ/ር ድሬ አካፍሉ" ብሏል፡፡

የዶ/ር ድሬ ፍሬ እንደሆነ የሚገለጸው ስኖፕ ዶግ በኢንስታግራም ላይ "ጨርሶ ይማርህ። ዶ/ር ድሬ እንፈልግሃለን" ብሏል።

ሚሲ ኢሊየት "ለዶ/ ር ድሬ እና ለቤተሰቦቹ በአዕምሮአቸው እና በአካላቸው ላይ እንዲድኑ እና እንዲጠናከሩ ጸሎቴ ይድረስ" ብላለች።

ሲያራ በትዊተር ገጹ ላይ "ዶ/ር ድሬ ሙሉ በሙሉ እንድታገገም እጸልያለሁ" ብላለች።

ዶ/ር ድሬ ከፕሮዲውሰርነት እና ትልቅ የሪከርድ ባለቤት ከመሆኑም በላይ እንደ ኤሚነም፣ 50 ሴንት እና ኬንድሪክ ላማር ያሉ አርቲስቶችን በማውጣቱም ይታወቃል።