በኢትዮጵያ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ቀረጥ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ ተደረገ

የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ በመሰረታዊ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ የቀረጥና የታክስ ማሻሻያ ማድረጓን የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ እንዳለው በዚህ ውሳኔ መሰረት የሴቶች ወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) እንዲሁም የህፃናት ንጽህና መጠበቂያ (ዳይፐር) በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ለምርታቸው በሚያስፈልጉና ከውጭ በሚያስገቧቸው የጥሬ እቃ ግብዓቶች ላይ የነበረው ታክስ እንዲነሳ መወሰኑን አመልክቷል።

በተጨማሪም እነዚህ የሴቶችና የህጻናት ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ከውጭ ተመርተው ሲገቡ ደግሞ ቀደም ሲል ተጥሎባቸው የነበረው የ30 በመቶ ከፍተኛ የታክስ ምጣኔ ተቀንሶ ወደ 10 በመቶ ብቻ እንዲሆን መደረጉን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ይህ የመንግሥት ውሳኔ እነዚህ መሠረታዊ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች በተለይም በወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማስቻልና የአገር ውስጥ አምራቾች እንዲበረታቱ የቀረጥና የታክስ ማሻሻያ መደረጉ ታውቋል።

ሚኒስቴሩ በተጨማሪም ይህ የቀረጥና ታክስ ማሻሻያ፣ ሴቶች የንጽህና መጠበቂያን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ በማድረግ ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከወር አበባ ጋር በተዛመዱ ምክንያቶች እንዳያቋርጡና በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ላይ የሥነ ልቦና ጫና እንዳይገጥማቸው ለማገዝ ነው ብሏል።

በተጨማሪም እርምጃው የአገር ውስጥ ምርትን በማሳደግና ዋጋ እንዲቀንስ በማድረግ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ችግር ዘላቂ በመሆነ መንገድ መፍታት እንዲሁም ጥራት ያላቸው ምርቶች እንዲቀርቡ ለማስቻል እንደሚያግዝ ተገልጿል።

በሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች አቅርቦት ዙሪያ በኢትዮጵያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በእነዚህ ምርቶች ላይ ባለው የዋጋ ውድነትና የአቅርቦት ችግር የተነሳ አብዛኞቹ ሴቶች የሚጠቀሙት በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ የወር አበባ መጠበቂያ ዘዴዎችን ነው።

ይህም በተለይ አብዛኛው ሕዝብ በሚኖርባቸው የገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች ትምህርትና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖን እንደሚያሳድር ይነገራል።

ለሴቶች መብት የሚሰሩ ማኅበራት፣ ተቋማትና ግለሰቦች የሴቶችን ጤናና ሁለገብ ተሳትፎ ለማበረታታት መንግሥት የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ዋጋ በእጅጉ የሚቀንሱ እርምጃዎችን እንዲወስድ ለዓመታት ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ ተጥሎ የቆየውን የቀረጥ ታክስ ለማንሳት እንዲሁም ለመቀነስ የወሰደችው እርምጃ በምርቶቹ ዋጋ ላይና አቅርቦት ላይ ጉልህ ውጤት እንደሚኖረው ይጠበቃል።

የገንዘብ ሚኒስቴር እንዳለው በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ስምንት የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) የሚያመርቱ ፋብሪካዎች አሉ።