የሮይተርሱ የካሜራ ባለሙያ ኩመራ ገመቹ ከእስር ተለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሮይተርስ የካሜራ ባለሙያ ኩመራ ገመቹ ከአስራ ሁለት ቀናት የእስር ቆይታ በኋላ መለቀቁን የሚሰራበት የዜና ተቋም አስታወቀ።
ፖሊስ የኩመራ ጠበቃ ለሆኑት መልካሙ ኦጎ፣ በጋዜጠኛው ላይ ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት፣ ከመንግሥት ጋር ከሚዋጉ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በማድረግ፣ እንዲሁም የሕብረተሰብን ሠላምና ደኅንነት በመረበሽ ጠርጥሮት በቁጥጥር ስር ማዋሉንና ምርመራ መጀመሩን ገልጾ ነበር።
ሮይተርስ በዘገባው ላይ ሁለት ሳምንት ለሚጠጋ ጊዜ በአስር ላይ የቆው የካሜራ ባለሙያው ኩመራ ገመቹ በምን ሁኔታ እንደተለቀቀ ያለው ነገር የለም።
"ኩመራ ተፈትቶ ከቤተሰቦቹ ጋር በመቀላቀሉ ደስተኞች ነን። ዛሬ መፈታቱ የሚያሳየን ምንም ዓይነት ጥፋት አለመፈፀሙን ነው" ብሏል የዜና ወኪሉ ከፍተኛ አርታኢ ስቴፈን ጄ አድለር።
በተጨማሪም "ኩመራ ሁሌም ሙያውን የሚያከብርና ተዓማኒነት ላለው መረጃ ራሱን የሰጠ፣ እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል ባልደረባነቱም ከኢትዮጵያ ነጻ፣ ገለልተኛና ከአድልኦ የፀዳ መረጃን ለማድረስ የሚተጋ ነው። እንደ ኩመራ ያለ ጋዜጠኛ ያለምንም ፍርሃትና መሸማቀቅ በየትኛውም ስፍራ ሕዝብ የሚፈልገውን መረጃ እንዲያደርስ መፈቀድ አለበት" ብሏል።
የኢትዮጵያ ፖሊስና አቃቤ ሕግ ቢሮዎች ኩመራ ለምን በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ሮይተርስ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም ነበር።
የ38 ዓመቱ ኩመራ ገመቹ ለሮይተርስ ከአስር ዓመት በላይ የሰራ የካሜራ ባለሙያ ሲሆን፤ ሐሙስ ዕለት ከሚከበረው የገና በዓል ቀደም ብሎ በመለቀቁ ቤተሰቡ ደስተኛ መሆኑን ተገልጿል።
ቤተሰቡ "ኩመራ በመፈታቱ ትልቅ እረፍት ነው የተሰማን፤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከጎናችን የነበሩትን ሁሉ እናመሰግናለን" ማለታቸውም ተገልጿል።
አክለውም "ኩመራ ምንም ጥፋት ያልሰራ ሙያውን አክባሪ እና ትጉህ ጋዜጠኛ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በነጻነት መዘገብ ብቻ ነው የሚፈልገው። በታሰረበት ወቅት ቤተሰቦቹ በጣም ናፍቀውት ነበር፤ ለገና በዓል ከቤተሰቡ ጋር በመቀላቀሉ እጅጉን ደስተኛ ነን።"
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በእስር ላይ የሚገኙ በርካታ ጋዜጠኞችን የለቀቁ ሲሆን፤ በአገር ውስጥ እንዳይነበቡ እና እንዳይታዩ ታግደው የነበሩ ከ250 በላይ የመገናኛ ብዙሃን እንዲከፈቱ እና በነጻነት እንዲሰሩ ፈቅደዋል።
ነገር ግን የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት ከሆነ የፌደራል መንግሥቱ ከህወሓት ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ከገባበት ጊዜ ወዲህ ጋዜጠኞች ላይ ወከባና እስር እየታየ መጥቷል።
የትግራይ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሰባት ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጋዜጠኛ መብት ተሟጋቾች ሪፖርት አድርገዋል።
የኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ ጋዜጠኛ ኡዲ ሙሳ፣ የዓል-ዓለም ጋዜጣ ሪፖርተር አብርሃ ሃጎስ፣ የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጠኞቹ ሃፍቱ ገብረእግዚአብሔርና ፀጋዬ ሃዱሽ በአሁኑ ወቅት በእሥር ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ሆነው ተመዝግበዋል።
ሌላኛው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን ሲፒጄ ኅዳር 22/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ሰባት ጋዜጠኞች በሰሯቸው ዘገባዎች ምክንያት እስር ቤት መግባታቸውን ገልጾ ነበር።
ከእነዚህ መካከል አምስቱ የታሰሩት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት ኃይሎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው።
ድርጅቱ ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2019 ጋር ሲነፃፀር ለጋዜጠኞች የተሻለ ነፃነት ሰጥታለች ይላል። አምና ከነበረችበት 119ኛ ደረጃም ወደ 99 ከፍ ማለት ችላለች።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የታየው የተስፋ ጭላንጭል እንዳይጨልም መንግሥት የጋዜጠኞችን ነፃነት ሊያስከብር ይገባል ይላል ማኅበሩ።














