ትግራይ ፡ ከውቅሮ ወጣ ብሎ በሚገኙ የእምነት ስፍራዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተገለፀ

በትግራይ ክልል ከውቅሮ ከተማ የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ወጣ ብሎ በሚገኘው ጥንታዊው የአል ነጃሺ መስጅድ እንዲሁም በአንድ ቤተክርስቲያን ላይ ጉዳት እንደደረሰ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በውቅሮ አል ነጃሺ መስጂድ እና በአማኑኤል ምንጉዋ ቤተክርስትያን ላይ ጉዳት መድረሱን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ጄይላን ከድር በመስጂዱ ላይ ስለደረሰው ጉዳት መረጃ እንዳልደረሳቸውና ከሁለት ቀናት በኋላ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአል ነጃሺ መስጂድ ጉዳት እንደደረሰበት መስማታቸውን ገልጸው፤ መስሪያ ቤታቸውም ወደ ሥፍራው የሚሄድ ሁለት የጥናት ቡድን እንዳዘጋጀ አመልክተዋል።
ይህ የጥናት ቡድን ወደ ትግራይ ወደ ስፍራው የሚሄደው በዕምነት ቤቶቹ ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን አጣርቶ ለጥገና የሚሆን መረጃ ለማሰባሰብ እንደሆነ ገልፀዋል።
የእስልምና ጉዳዮች ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በአካባቢው ካሉ የሐይማኖት አባቶች ጋር ግንኙነት በማድረግ ስላለው ሁኔታ ለማወቅ ባለመቻሉ ስለጉዳቱ ለማረጋገጥ እንዳልቻለ ዶ/ር ጄይላን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጄላን ለቢቢሲ እንዳሉት ይህ የአምልኮ ስፍራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ቅርስ በመሆኑ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ የደረሰው ጉዳት ይገለፃል ሲሉ ተናግረዋል።
እነዚህ የሐይማኖት ስፍራዎች ከቅርስ ባሻገር የአምልኮ ስፍራዎች ናቸው ያሉት ምክትል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ተጠግነው ወደ አገልግሎት መመለስ አለባቸው ሲሉ ያስረዳሉ።
ወደ ትግራይ ውቅሮ የሚሄደው ቡድን ሁለት መሆኑን የሚናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ አንደኛው የትግራይ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮን የሚያካትት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከፌደራል መንግሥቱ ተዋቅሮ የሚሄድ ቡድን ነው።
ጨምረውም ለቢቢሲ ስለጉዳዩ ሲያስረዱ ባለሙያዎች ቀደም ብሎ ሊሄዱ አስበው አለመሳካቱን በመግለጽ፣ አሁን ግን የባሕል ሚኒስትሯ የሚያዋቅሩት ቡድን መኖሩንና ከቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ከሚያዋቀረው ቡድን ጋር በመሆን ወደ ሥፍራው በማቅናት አል ነጃሺ መስጂድን እንዲሁም ሌሎች ስፍራዎችን ተመልክቶ እንደሚመጣ ተናግረዋል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ከሆነ በውቅሮ አል ነጃሺ መስጂድ ላይ ብቻ ሳይሆን አማኑኤል ምንጉዋ የተባለ ቤተክርስቲያንም በተመሳሳይ መንገድ ጉዳት እንደደረሰበት መስማታቸውን ገልፀው፤ መጀመሪያ በውቅሮ አካባቢ ባሉት እነዚህ የእምነት ተቋማትና ቅርሶች ላይ የደረሰውን ጉዳት ተመልክቶና አጣርቶ የሚመጣ ቡድን እንደሚላክ አሳውቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, FB
ሁለተኛው ቡድን ደግሞ በስፍራዎቹ ስላሉ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ባለው መረጃ መሠረት፣ በቦታቸው አሉ ወይስ የሉም የሚለውን መረጃ ለማጣራት እንደሚላክም ገልፀዋል።
"በእንዲህ አይነት ግጭት ወቅት ከቋሚ ቅርሶች በበለጠ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ ጉዳት ይደርሳል" ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ እነዚህን ቅርሶች አጣርቶ የሚመጣ ቡድን እንደሚላክ አረጋግጠዋል።
የመጀመሪያው ቡድን ወደ አካባቢው የሚሄደው ጥር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
ብሔራዊው ቴሌቪዥን ኢቲቪ ሰኞ ምሽት በነጃሺ መስጂድና በአቅራቢያው በሚገኘው አማኑኤል ቤተክርስቲያን ላይ ስለደረሰው ጉዳት የአካባቢውን ነዋሪዎች በማናገር ባቀረበው ዘገባ የህወሓት ኃይሎች በስፍራው ምሽግ መስራታቸውንና ለደረሰው ጉዳት ምክንያት መሆናቸውን አመልክቷል።
በትግራይ ክልል የተካሄደውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ ለረጅም ጊዜ መረጃ ለማግኘት አዳጋች ሆኖ የቆየ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ታሪካዊው የአል ነጃሺ መስጂድ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት የሚያሳዩ ፎቶግራፎች በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ በስፋት ሲዘዋወሩ ቆይተዋል።
በዚህ ዙሪያ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርም ሆነ ፌደራል መንግሥቱ እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የሌለ ሲሆን ተቃዋሚዎቹ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በጉዳዩ ላይ መግለጫ አውጥተዋል።
ኢዜማ ባወጣው መግለጫ በአል ነጃሺ መስጂድ ላይ የደረሰው ጥቃት በገለልተኛ አካላት በፍጥነት እንዲጣራና ጥንታዊ ቅርስነቱን ሳይለቅ ወደነበረበት ሁኔታ በፍጥነት እንዲመለስ ጥሪ አቅርቧል።
አብንም በበኩሉ አል ነጃሺ መስጅድ ላይ የደረሰው ጥቃት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በገለልተኛ መልኩ በጥልቀት መመርመር እንዳለበትና እንዲጣራ ጠይቋል።
ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ጥንታዊው የአል ነጃሺ መስጂድ ከሁለት ዓመት በፊት በቱርክ መንግሥት ድጋፍ ጥገና ተደርጎለት እነደነበር ይታወሳል።
በ4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው አል ነጃሺ መስጂድ ዋነኛ የፀሎት ቦታ እና ሁለት የቀብር ስፍራን መያዙ ይነገራል።
ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም ከባሕር ማዶ ስፍራውን ለማየት፣ መውሊድንና ረመዳንን ለማክበር የሚመጡ ሰዎችን ለማሳረፍ በማሰብ ማረፊያ ክፍሎችም ተገንብተዋል።












