ኮሮናቫይረስ፡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ የተጎዳችው ብራዚል ክትባት መስጠት ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የብራዚል ጤና ቁጥጥር መሥሪያ ቤት ሁለት የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባቶች ለዜጎቹ እንዲሰጡ ካፀደቀ በኋላ የመጀመሪያውን ክትባት አንዲት ነርስ መከተቧ ተገለጸ።
አንቪሳ፣ የብራዚሉ ጤና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ እውቅና የሰጣቸው ክትባቶች የኦክስፎርዱ አስትራዜኔካ እና የቻይናው ሲኖቫክ ክትባቶች ናቸው።
ክትባቱን የወሰደችው የ54 ዓመቷ ነርስ፣ ሞኒካ ካላዛንስ የምትባል ስትሆን የሳኦ ፖሎ ነዋሪ ነች።
እነዚህ ሁለቱ ክትባት በብራዚል 27 ግዛቶች በሙሉ ተሰራጭተዋል ተብሏል።
ብራዚል የኮሮናቫይረስ ክትባትን መስጠት የጀመረችው ከአህጉሩ አገራት በሙሉ ዘግይታ ነው።
ብራዚል በከፍተኛ ሁኔታ በኮሮናቫይረስ ስርጭት የተጎዳች ስትሆን በተህዋሲው ምክንያት በሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከዓለም ሁለተኛዋ ነች።
በብራዚል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት የሚያደርሰውን ጉዳት ያጣጥሉ የነበሩት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ፣ አገራቸው በሁለተኛ ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስትጠቃ ዳግም ተቺዎቻቸው እያብጠለጠሏቸው ይገኛሉ።
እሁድ ዕለት ብቻ 551 ሰዎች በወረርሽኙ ሰበብ መሞታቸው የተመዘገበ ሲሆን ከስድስት ቀን ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሟቾች ቁጥር ከ1000 በታች የተመዘገበበት ዕለት ነው ተብሏል።
በብራዚል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ 209,000 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሲሞቱ፣ ይህም አጠቃለይ ከአሜሪካ በመቀጠል በዓለማችን ላይ ሁለተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
በአገሪቱ 8.4 ሚሊየን ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ ሲታወቅ ይህም በዓለም ላይ ሦስተኛዋ አገር ያደርጋለታል።
የጤና ሚኒስትሩ ኤድዋርዶ ፓዙኤሎ በአገራቸው የሚሰጠው የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት፣ ክትባቱን በአገር ውስጥ እንዲያመርቱ ፈቃድ በተሰጣቸው ሁለት የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ይታገዛል ብለዋል።















