ኮሮናቫይረስ ፡ ሲሼልስ የኮቪድ -19 ክትባት መስጠት ጀመረች

የሲሼልስ ፕሬዚደንት ዋቨል ራምካላዋን

የፎቶው ባለመብት, AFP

በርካቶች ለመዝናናት የሚመርጧት አፍሪካዊቷ ደሴታማ አገር፣ ሲሼልስ የኮሮናቫይረስ ክትባት መስጠት መጀመሯን አስታወቀች።

ይህንን በማድረግም ከጊኒ ቀጥላ ሁለተኛዋ አፍሪካዊት አገር ሆናለች። ጊኒ የሩሲያውን ስፑትኒክ ቪ ክትባት አነስተኛ ዶዝ ያገኘችው ባለፈው ወር ነበር።

የሲሼልስ ፕሬዚደንት ዋቨል ራምካላዋን ዕሁድ እለት የመጀመሪያውን ክትባት በቀጥታ ቴሌቪዥን ሥርጭት እየታዩ ተከትበዋል።

ፕሬዚደንቱ "የተሰማኝ ልክ እንደማንኛውም ክትባት ነው" በማለት ሌሎች ሰዎች ክትባቱን እንዲወስዱ አበረታተዋል።

ደሴታማዋ አገር ሲሼልስ ቻይና ያበለፀገችውን ክትባት ከተባበሩት አርብ ኤምሬትስ 50 ሺህ ዶዝ [መጠን] በእርዳታ አግኝታለች።

ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ዛሬ የጤና ባለሙያዎች መከተብ እንደሚጀምሩ እና ከዚያ በኋላ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ክትባቱን እንደሚወስዱ ተናግረዋል። ይህ ሲጠናቀቅም ክትባቱ ለሌሎች ሕዝቦቿ ይዳረሳል ተብሏል።

አገሪቷ ከሁለት ወር እስከ ሦስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ካሏት 98 ሺህ ሕዝብ 70 በመቶውን ለመከተብ አቅዳለች። ይህንን ለማሳካትም በአንድ ቀን 1 ሺህ ሰዎችን መከተብ ይጠይቃል።

ሲሼልስ እስካሁን 508 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን ያስተናገደችው አንድ ሞት ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ባለሥልጣናት በቅርቡ የታየው የቫይረሱ ሥርጭት አስግቷቸዋል። ቅዳሜ ዕለት ብቻ በአገሪቷ 57 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጿል።