በኢንዶኔዢያ መሬት መንሸራተት ነፍስ ለማዳን የተሰማሩ ሠራተኞች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በኢንዶኔዢያ በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት የተጎዱትን በመፈለግ ላይ የነበሩ የነፍስ አድን ሠራተኞች ሁለተኛ ዙር በተከሰተ የመሬት ናዳ ተጭኗቸው መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
መጀመሪያው በዌስት ጃቫ ቺያንጁዋንግ መንደር በጣለ ከባድ ዝናብ ሳቢያ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከስቶ ነበር።
ሌላኛው አደጋ ደግሞ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው እየወጡ ባለበት ሰዓት የተከሰተ ነው። በአደጋውም ቢያንስ 12 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በርካቶች የደረሱበት አልታወቀም።
በኢንዶኔዢያ በዝናብ ወቅት የመሬት መንሸራተት አደጋ የተለመደ ሲሆን፤ የደን መጨፍጨፍ ለዚህ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።
በቅርብ የተከሰተው አደጋ ከዋና ከተማዋ ጃካርታ 150 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሰሜዳንግ የሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።
የአደጋ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ራዲይታ ጃቲ በመግለጫቸው እንደተናገሩት አደጋዎቹ ያጋጠሙት በ3፡30 ሰዓት ልዩነት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Antara Foto/Novrian Arbi/Reuters
ቃል አቀባዩ የመጀመሪያው አደጋ የተከሰተው በከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ የአፈር መሸርሸር ሳቢያ ሲሆን፤ ቀጣዩ ደግሞ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በመጀመሪያው አደጋ የተጎዱትን ለማውጣት እየሰሩ ባለበት ወቅት ያጋጠመ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ አደጋም የነፍስ አድን ሠራተኞቹ ከሞቱት መሃል እንደሚገኙበት ቃል አቀባዩ አክለዋል። የ6 ዓመት ሕጻንም ከሟቾቹ መካከል እንደሚገኝበት ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
እሁድ ዕለት 27 ሰዎች የደረሱበት እንዳልታወቀ እና 46 የሚሆኑት ከአደጋው መትረፋቸውን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በአካባቢው ያለው ከባድ የአየር ሁኔታም የነፍስ አድን ሥራውን እንዳስተጓጎለው የተገለፀ ሲሆን ፍለጋው ዛሬ ይቀጥላል ተብሏል።












