ሕዳሴ ግድብ፡ ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት ላይ ሳትስማማ ቀረች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲያደርጉት የነበረው ውይይት በሳምንቱ ማብቂያ ላይ የተሰበሰበ ሲሆን ድርድሩን ለማስቀጠል በቀረበ ሃሳብ ላይ ሱዳን ሳትስማማ መቅረቷን ተገለጸ።
ድርድሩን ለማስቀጠል እንዲያግዝ አገራቱ ከአፍረካ ሕብረት ባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ ካካሄዱ በኋላ ውጤቱ ለሕብረቱ ምክር ቤት ሊቀመንበር እንዲቀርብ በሚለው ሃሳብ ላይ ኢትዮጵያና ግብጽ ሲስማሙ ሱዳን እንዳልተቀበለችው ስለሚኒስትሮቹ የሦስትዮሽ ስብሰባ የወጣው መግለጫ አመላክቷል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ እየገነባችው ያለው ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታው 78 በመቶ ያህል መድረሱ የተነገረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ማካሄዱ ይታወሳል።
ቀደም ሲል ተጀምሮ ሲካሄድ የነበረው በግድቡ የውሃ ሙሌትና ቀጣይ ሥራ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት የሚካሄደው ውይይት፤ እሁድ ዕለት በሦስቱ አጋራት ሚኒስትሮች መካከል በበይነ መረብ የተካሄደ ሲሆን መግባባት ላይ ሳይደረስ መጠናቀቁ ተገልጿል።
ይህ ስብሰባ የአፍሪካን ሕብረት በመወከል በደቡብ አፍሪካ የዓለምአቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ሕብረት አስፈጻሚ ምከር ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢ ናሌዲ ፓንዶር የሚመራ ሲሆን፣ እርሳቸውም ስብሰባው ያለስምምነት በመጠናቀቁ ማዘናቸውን እና ጉዳዩን ወደ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ እንደሚመሩት ማስታወቃቸውን የሱዳን የዜና ወኪል ዘግቧል።
ሱዳን በበኩሏ የሕዳሴ ግድብ ስምነቱ መቋጫ ሳያገኝ ሁለተኛ ዙር ሙሌት የሚካሄድ ከሆነ በሮዚየር ግድብ ላይ አደጋ መደቀኑን በማንሳት ተቃውማለች።
ሮዚየር ግድብ ውሃ የመያዝ አቅሙ ከሕዳሴ ግድብ በ10 በመቶ ያነሰ ነው ተብሏል።
የሱዳን ዜና ወኪል የአገሪቱን የመስኖና ውሃ ሀብቶች ሚኒስትርን ፕሮፌሰር ያሲር አባስን ጠቅሶ እንደዘገበው አገራቸው የሕዳሴ ግድብ አደራዳሪዎቹ ያለውን ልዩነት ማጥበብ እንዲችሉ ሚናቸው እንዲሰፋ እንደምትፈልግ መግለጻቸውን ዘግቧል።
ግብጽ በተደጋጋሚ ግድቡ የውሃውን መጠን ይቀንሰዋል ስትል ቅሬታ ስታሰማ ቆይታለች።
ትናንት የተካሄደው ስብሰባ ባለፈው ሳምንት እንዲካሄድ ስምምነት ተደርሶበት የነበረው የሦስትዮሽ ስብሰባ ቀደም ባለው ውይይት ላይ ሱዳን ሳትገኝ በመቅረቷ ምክንያት ሳይካሄድ ከቀረ በኋላ የተካሄደ ነው።
የአፍሪካ ሕብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ድርድሩን ለማስቀጠል ይረዳል በሚል አገራቱ ለሦስት ቀናት ከአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ እንዲያካሂዱ፣ በማስከተል የሦስትዮሽ ስብሰባ እንዲካሄድ እና ውጤቱ ለሊቀመንበሯ እንዲገለጥ ሃሳብ አቅርበው እንደነበር የወጣው መግለጫ ያሳያል።
"ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ይህን ተቀብለው በውይይቱ ለመቀጠል የተስማሙ ሲሆን ሱዳን ሃሳቡን ባለመቀበሏ ስብሰባው በዚሁ ተጠናቋል" ይላል መግለጫው።
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ስብሰባ ሱዳን የሦስትዮሽ ስብሰባ እንዳይካሄድ እና ስብሰባዎች ከአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ጋር ብቻ እንዲደረጉ አቋም መያዟ ይታወሳል።
ሆኖም በአሁኑ ስብሰባ አገራቱ ከአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ ያድርጉ የሚለው ሃሳብ ሲቀርብ፣ ሱዳን የባለሙያዎቹ የተጨማሪ ኃላፊነት መመሪያ (ቢጋር) ካልተዘጋጀ በቀር መካሄድ አይችልም የሚል አቋም መያዟን በመግለጫው ላይ ገልጿል።
ኢትዮጵያ የሱዳንን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲቻል በግድብ ደኅንነት፣ በመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በሌሎች ቴከኒካዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሄ ለመስጠት ዝግጁነቷን መግለጿን አስታውቃለች።
ሲጠናቀቅ የአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ይሆናል የተባለው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ ሱዳንና ግብጽ ቅሬታ በማንሳታቸው ይህንኑ በውይይት ለመፍታት ተከታታይ ድርድሮች ሲደረጉ ቆይተዋል።
ምንም እንኳን ሁለቱ አገራት የውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ስምምነት መደረስ አለበት በማለት ግፊት ቢያደርጉም ኢትዮጵያ ባለፈው የክረምት ወር የግድቡን የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ ማከናወኗን መግለጿ ይታወሳል።
ግብጽ ከአባይ ወንዝ ላይ በማገኘው የውሃ መጠን ላይ መቀነስን ያስከትላል በሚል ጥያቄ በምታነሳበት በዚህ ግድብ ዙሪያ በአዲስ አበባ፣ በካርቱም፣ በካይሮና በዋሽንግተን ውስጥ አገራቱ ተከታታይ ድርድሮች ቢካሄዱም አስካሁን መደምደሚያ ላይ አልተደረሰም።
በተለይ በአሜሪካ አሸማጋይነት ዋሽንግተን ላይ ሲካሄድ የነበረው ድርድር መቋጫ ላይ ይደርሳል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም በመጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ ጥቅሜን የሚያስጠብቅ አይደለም በማለት ራሷን ከስምምነቱ ውጪ ማድረጓ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የተጀመረው ውይይት እየተካሄደ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች እየተቋረጠ መልሶ ሲጀመር እዚህ ላይ ደርሷል።















