ኮሮናቫይረስን ፈርቶ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ 3 ወር የተደበቀው ግለሰብ ታሰረ

ኮሮናቫይረስን ፈርቶ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ 3 ወር የተደበቀው ግለሰብ ታሰረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አዲታ ሲንግ የተባለ ግለሰብ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ይይዘኛል ብሎ ፈርቶ ለሦስት ወራት የቺካጎ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ተደብቆ እንደነበር የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

የ36 ዓመቱ ግለሰብ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ለሦስት ወራት ሲደበቅ ማንም አላስተዋለውም ነበር። ነገር ግን ቅዳሜ እለት አንድ የአውሮፕላን ማረፊያው ሠራተኛ የጉዞ ሰነድ እንዲያሳይ ጠይቆት ተጋልጧል። በቁጥጥር ስርም ውሏል።

ግለሰቡ ማንነቱን የሚያሳይ ሰነድ እንዲያሳይ ሲጠየቅ ያቀረበው አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ የሚሠራ ግለሰብን መታወቂያ ነበር። ይህ ሠራተኛ ጥቅምት ላይ መታወቂያው እንደጠፋ አመልክቶ ነበር።

ፖሊስ እንዳለው አዲታ ጥቅምት 19 ከሎስ አንጀለስ፤ ቺካጎ ከገባ በኋላ ከአውሮፕላን ማረፊያው አልወጣም።

የአውሮፕላን ማረፊያው ሠራተኛን መታወቂያ አግኝቶ እንደወሰደ ተናግሯል። ኮሮናቫይረስ ሊይዘኝ ይችላል ብሎ ፈርቶ ወደ ቤቱ እንዳልተጓዘም ተገልጿል።

ቺካጎ ትሪቢውን የዓቃቤ ሕግ አባል ካትሊን ሀግርቲን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ግለሰቡ ከተጓጓዦች እርዳታ እየጠየቀ 3 ወር ኖሯል።

ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ሱዛና ኦርቴዝ መገረማቸውን ገልጸው "የአውሮፕላን ማረፊያው ሠራተኛ ያልሆነ ግለሰብ ከጥቅምት 19 እስከ ጥር 16 ድረስ ማንም ሳይደርስበት አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ኖረ ማለት ነው?" ሲሉ ዐቃቤ ሕግን ጠይቀዋል።

ግለሰቡ የሎስ አንጀለስ ነዋሪ ነው። ከዚህ ቀደም ምንም ወንጀል እንዳልሠራ ተገልጿል። ለምን ወደ ቺካጎ እንዳቀና ግን ግልጽ አይደለም።

ከውሮፕላን ማረፊያ ሠራተኞች ውጪ ክልክል በሆነ ቦታ በመገኘትና በአነስተኛ ስርቆት ክስ ተመስርቶበታል።

በ1,000 ዶላር ዋስ ከእስር እንደሚለቀቅና ከዚህ በኋላ ወደ አውሮፕላን ማረፊያው መግባት እንደማይችል ተዘግቧል።

ዳኛዋ፤ ተጓጓዦች ደህንነት እንዲሰማቸው የአውሮፕላን ማረፊያዎች ጥበቃ አስተማማኝ መሆን አንዳለበት ተናግረዋል።

"ግለሰቡ የፈጸመው ተግባር ለማኅበረሰቡ አደገኛ ያደርገዋል" ሲሉም ተደምጠዋል።

የቺካጎን አውሮፕላን ማረፊያዎች የሚቆጣጠረው አቪየሽን ክፍል "ጉዳዩን እየመረመርን ቢሆንም ግለሰቡ በተጓዦችም ይሁን በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ የጸጥታ ችግር እንዳልፈጠረ አረጋግጠናል" ሲል መግለጫ አውጥቷል።