ኮሮናቫይረስ፡ አፍሪካ 270 ሚሊዮን 'ዶዝ' የኮቪድ-19 ክትባት አገኘች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አፍሪካ ለአህጉሩ የሚሰራጭ ለጊዜው 270 ሚሊዮን 'ዶዝ' (መጠን) የኮቪድ-19 ክትባት በአፍሪካ ሕብረት በኩል ማግኘቷ ተገለፀ።
አጠቃላይ የተገኘው ክትባት በዚህ ዓመት ጥቅም ላይ እንደሚውል የሕብረቱ መሪ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ ቃል ገብተዋል።
ይህ ክትባት ከዚህ ቀደም ቃል ከተገባው 600 ሚሊየን 'ዶዝ 'ተጨማሪ ቢሆንም አሁንም ግን ሙሉ አህጉሩን ለመከተብ በቂ አይደለም።
በዚህም የዓለማችን ድሃ አገራት ከሃብታም አገራት ይልቅ ክትባቱን ለመከተብ ረዥም ጊዜ ሊጠብቁ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
ምንም እንኳን በአፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በንፅፅር ዝቅተኛ ቢሆንም በአንዳንድ አገራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በድጋሜ እየጨመረ ነው።
በደቡብ አፍሪካ አዲሱ የኮቪድ -19 ዝርያ ስጋት የፈጠረ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎችም በዚሁ ቫይረስ እየተያዙ ነው።
"በዚህ ምክንያት በጥረታችን ለጊዜው 270 ሚሊየን ዶዝ [መጠን ] ክትባት ከሦስት የክትባት አቅራቢዎች ማለትም ፋይዘር፣ አስትራዜኔካ[ በሕንድ ሴረም ኢንስቲቲዩት በኩል] እና ከጆንሰን እና ጆንሰን አግኝተናል" ብለዋል ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ ረቡዕ ዕለት በሰጡት መግለጫ።
ቢያንስ 50 ሚሊዮን 'ዶዝ' [መጠን] ክትባቶችም ወሳኝ በሆኑት ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ባሉት ወራት እንደሚቀርቡ ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ቀጠናው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገራት ክትባቱን ማዳረስ አላማ ካደረገው ግሎባል ኮቫክስ 600 ሚሊየን ዶዝ [መጠን] እንደሚጠብቅ ተገልጿል።
ይሁን እንጂ በአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል የሳይንስ አማካሪ የሆኑት ኒካሴ ደምቢ "አማራጭ መፍትሔ ስላለን ደስተኞች ነን" በማለት ባለሥልጣናት አሁንም ዝርዝር ጉዳዮችን እየተጠባበቁ መሆኑን ለኤአፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ፕሬዚደንት ራማፎሳ እንዳሉት ባለሥልጣናት በኮቫክስ ጥረት በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የመጀመሪያ ዓመት አጋማሽ የተለቀቀው ክትባት የጤና ባለሙያዎችን ለመከተብ ብቻ በቂ ነው የሚል ስጋት አላቸው።
እያንዳንዱ ሰው ሁለት ዶዝ ክትባት መውሰድ ያለበት ሲሆን 1.3 ቢሊዮን ሕዝብ ያለውን አህጉር አፍሪካ ለመከተብ 2.6 ቢሊየን ክትባት ያስፈልጋል።
"እነዚህ ጥረቶች፤ የኮቫክስ ጥረቶችን ለመደጎም እና ብዙ የክትባት ዶዞችን በተቻለ መጠንና ፍጥነት በመላው አፍሪካ እንዲዳረስ ለማረጋገጥ ነው" ሲሉ ፕሬዚደንቱ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አብራርተዋል።
አፍሪካ እስካሁን ከ3 ሚሊዮን በላይ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡባት ሲሆን 75 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችም በበሽታው ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።
በአንጻሩ ደግሞ አሜሪካ 23 ሚሊዮን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችና ከ383 ሺህ በላይ ሞት ተመዝግቦባታል።
የዓለም አገራት ክትባቱን ለመግዛትም ጥድፊያ ላይ ናቸው። ሃብታም አገራትም አብዛኛውን በክትባት አምራቾች የቀረበውን ክትባት በመግዛታቸው ክስ ይቀርብባቸዋል።












