ኮሮናቫይረስ፡ ብራዚል ቻይና ሰራሹ የኮሮቪድ-19 ክትባት ውጤታማነቱ 50.4 በመቶ ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቻይናው ሲኖቫክ የተመረተው የኮሮናቫይረስ ክትባት በብራዚል ቤተሙከራዎች ውስጥ ተፈትሾ 50.4 በመቶ ብቻ ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ።
የዚህ ክትባት ውጤታማነት ከዚህ ቀደም ይፋ በተደረገው መረጃ መሰረት ከፍ ያለ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የብራዚል ተመራማሪዎች 50 በመቶን ያለፈው ለጥቂት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የብራዚል መንግሥት ለዜጎቹ ለመስጠት ካዘጋጃቸው ሁለት ክትባቶች መካከል የቻይናው አንዱ ነበር።
ብራዚል በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት መካከል አንዷ ናት።
ሲኖቫክ መቀመጫውን ቻይና ቤይጂንግ ያደረገ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ሲሆን፣ ኮሮናቫክ የተሰኘ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትን ማምረቱ ተገልጿል። ክትባቱ የተሰራው ከሞቱ የተህዋሲው አካላት ሲሆን፣ ያለምንም ተጨማሪ ሕመም ሰውነትን ለቫይረሱ በማጋለጥ የመከላከል አቅምን ያዳብራል ተብሎ ነበር።
ይህ ኩባንያ ያመረተውን ክትባት ኢንዶኔዢያ፣ ቱርክ እና ሲንጋፖር ማዘዛቸውም ተሰምቷል።
ባለፈው ሳምንት የቡታንታን ምርምር ማዕከል ተመራማሪዎች፣ በብራዚል የክትባቱን ውጤታማነት የፈተሹ ሲሆን፤ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ከመካከለኛ እስከ የከፋ ምልክት ያሳዩ ሰዎች ላይ 78 በመቶ ውጤታማ ነው ብለው ነበር።
ነገር ግን ማክሰኞ ዕለት ተመራማሪዎቹ ከዚህ ቀደም ይፋ ያደረጉት ውጤት የሕክምና ተቋም እርዳታ ፈልገው ያልመጡ እና "በጣም መካከለኛ ሕመም" ያለባቸውን ሰዎች መረጃ አለማካተቱን ገልፀዋል።
ይህ መረጃ ሲካተትም የክትባቱ ውጤት 50.4 በመቶ ነው ብለዋል ተመራማሪዎቹ።
ነገር ግን የቡታንታን ተመራማሪዎች አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት ከሆነ፣ የሕክምና ክትትል የሚፈልጉ መካከለኛ ህመም ያለባቸው ሰዎች ላይ የመከላከል አቅሙ 78 በመቶ ሲሆን፣ ከመለስተኛ እስከ ጽኑ ህሙማን ላይ ደግሞ እስከ መቶ በመቶ የመከላከል አቅም አለው ብለዋል።
የሲኖቫክ ክትባት በተለያዩ አገራት በተደረገለት ፍተሻ የተለያዩ ውጤቶችን አሳይቷል።
ባፈው ወር የቱርክ ተመራማሪዎች የሲኖቫክ ክትባት 91.25 በመቶ ውጤታማ ነው ያሉ ሲሆን፤ ከዛሬ ጀምሮ በጅምላ ክትባቱን የምትሰጠው የኢንዶኔዢያ ተመራማሪዎች ደግሞ 65.3 በመቶ ውጤታማ ነው ብለዋል።
ቻይና የሰራችው የኮሮናቫይረስ ክትባት ምዕራባውያኑ እንደፈበረኳቸው ክትባቶች ተገቢው ፍተሻ እና ክትትል አልተደረገበትም በሚል ወቀሳ ይቀርብበታል።
ይሁን እንጂ ብራዚል በኦክስፎርድ የተመረተው የአስትራዜኔካን እና የሲኖቫክ ክትባቶችን ለአስቸኳይ ጊዜ ለመጠቀም የአገሪቱ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንን ፈቃድ እየጠበቀች ነው።
ብራዚል በኮሮናቫይረስ በተያዙ ሰዎች ብዛት ከአሜሪካ እና ከሕንድ በመቀጠል ሦስተኛዋ አገር ናት።
8.1 ሚሊዮን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ያሉባት ብራዚል ክትባቱን መቼ መስጠት እንደምትጀምር የታወቀ ነገር የለም።















