ምዕራብ ጎንደር ዞን፡ መንገደኞችን በማገት በመቶ ሺህዎች የሚጠይቁት ሽፍቶች

የኢትዮጵያ ካርታ

የፎቶው ባለመብት, Google Map

ከሳምንታት በፊት የምዕራብ ጎንደር ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የዞኑን የህዝብና ሰላምና ደኅንነት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አራጋው አዛናውን ጠቅሶ በአካባቢው እገታ መፈጸሙን አስታውቆ ነበር።

"በቀን 16/06/13 ከጧቱ ሁለት ሰአት አካባቢ ከሽንፋ ወደ ገንዳ ውሃ ሲጓዝ የነበረን ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ በመተማ ወረዳ በለምለም ተራራና ጉባይ ቀበሌዎች አዋሳኝ ቦታ ሽፍቶች የዝርፊያ እና የእገታ ወንጀል ፈጽመዋል።" ብሏል።

አጋቾቹ አንድ የፖሊስ አባል ገድለው፤ ግለሰቦችን አግተው በመቶ ሺህ ብሮች እየጠየቁ ነው ፤ በርካታ ንብረትም ዘርፈዋል ሲል አስታውቋል።

ቢቢሲ በወቅቱ ታግተው ከነበሩ ግለሰቦች መካከል ሶስቱን አግኝቶ ስለነበረው ሁኔታ ማናገር ችሏል።

"እያገላበጡ እንደገብስ ወቁኝ"

ከአራቱ ታጋቾች አንዱ የሆነው መለሰ የኔዓለም "መረጃ ስላላቸው እኔ ባልሄድ እነሱም አይያዙም ነበር" ሲል የነበረውን ሁኔታ ማስረዳት ይጀምራል።

አጋቾቹ ሰኞ ይመጣል የሚል መረጃ እንደነበራቸው እና ሰኞ ሲቀር ማክሰኞ እንደጠበቁት ይገልጻል። ከፊት ለፊታቸው ሲሄዱ የነበሩ ስድስት መኪኖችን አልፈው እነሱን ማስቆማቸውንም መረጃ አላቸው ብሎ እንዲደመድም ምክንያት ሆኖታል።

"ጠንካራ መረጃ እዚህ [ሸንፋ ከተማ] አላቸው። ከቤቴ ስወጣም የሚከታታለኝ አለ። [ተይዘን] ሹፌሩን አስወርደው ካበቁ በኋለ ከሴቶች በስተጀርባ ሲፈትሽ ሲያጣኝ ወረደ። ሁለተኛ ጊዜም ሲያጣኝ በስልክ ጠይቆ ነው መጋረጃውን መንጥቆ የወሰደኝ" ብሏል።

ተቀጥሮ እንደሚሠራ በተደጋጋሚ ቢነግራቸውም ነጋዴ መሆኑን እና ለዚህ መረጃ እንዳላቸው በመግለጽ ደጋግመው ገርፈውታል።

" ሾፌሩም ተገርፏል፤ ግን ልዩነት አለው። ግርፋታቸው ብዙ አይደለም እንደኔ የጠነከረ ግርፋት የላቸውም። ነጋዴ ነው ብር አለው በሚል ነው" ብሏል መለሰ።

"በሰደፍም መትተውኛል። እንደገናም ሌዛ የሚባል እንጨት አለ ያንን ቆርጠው ለቁም እያገላበጡ ወቁኝ። እንደገብስ እንደኑግ አለ አይደል? 'ስላንተ የተለየ መረጃ እየሰማን ነው። መረጃህ እንደዚህ [ነጋዴ ነው። ገንዘብ አለው] እያለን ነው አንተ እንዴት ትደብቀናለህ? እኔ ተቀጥሬ እሠራለሁ ትላለህ። የሚነግረን መረጃ ንብረቱ ያንተ ነው እንጂ ተቀጥረህ በውክልና እየሠራህ አይደለም የሚል ነው' በሚል ነው የገረፉኝ።"

ከመኪና ካስወረዷቸው በኋላ ገንዘብ፣ ስልክ፣ ቀለበት እና የአንገት ማህተብ ጭምር ወስደውበታል። "ሽርጤንም 'የሰው ነው ብዬ ነው' ያስቀረሁት- በሙሉ የቀረ ነገር የለም ከኪሴ" ብሏል።

መኪናው ላይ ተጭኖ የነበረው የጓደኛው አኩሪ አተር ነበር። እህሉንም ምንም አላዳረጉም። "በመረጃ የኔን መሄድ ነው እንጂ የሚፈለጉት ከእህሉ አይደለም ጉዳዩ። ከዚህ [ከከተማ] ያለው መረጃ እኔ ባለሃብት መሆኔን 'ብር ያለው እሱ ነው' በማለት ይነግራቸው ነበር" ሲል ያስረዳል።

በሌላ መኪና ውስጥ የነበረ የጸጥታ አባል ከቦታው ደርሶ ከአጋቾቹ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የአንድ አጋች ህይወት ሲያልፍ የጸጥታ አባሉም ሞቷል።

ቢቢሲ መለሰን ለማናገር በመጀመሪያው ቀን ያደረገው ሙከራ ግርፊያው ባደረሰበት ህመም ምክንያት ሊሳካ አልቻለም። በሁለተኛው ቀን ቃለ መጠይቁን ሲያደርግ በተደጋጋሚ ህመሙን ቻል አድርጎ መረጃውን ለመስጠት ካለው ፍላጎት ማውራቱን ገልጿል።

ትከሻው እና ኩላሊቱ አካባቢ በደረሰበት ምት በሚሰማው ህመም ምክንያት በሆዱ እንደሚተኛ ገልጿል።

ከአጋቾቹ ጋር ያሳለፉትን አራት ቀናት "ማደሪያ የለንም። መንገድ ነው የምናድረው። ቀን ምሽግ ነው የምንውል። አለ አይለደል ዋሻ ውስጥ ነው የሚያውሉን" ሲል ያስታውሳል።

"ለእነሱ ለምለም እንጀራ ይመጣላቸዋል። ለእኛ የሠርግ ኮሾሮ [የእንጀራ ድርቆሽ] በኩባያ ይሰጡናል። በቀን አንድ ጊዜ አንድ ኩባያ ለአራት ይሰጡናል" ይላል።

እንደ መለሰ ከሆነ አጋቾቹ ያሉበት ቦታ እንዳይታወቅም ሱዳን ድንበር አካባቢ መሆናቸውን በመጥቀስ ለቤተሰቦቻቸው ሲነግሩ ነበር።

ቤተሰቦቹ እንዲለቀቅ ከፈለጉ ከ450 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል።

ቤተሰቦቹ ጉዳዩን ለህግ አካላት ለማሳወቅ ሲንቀሳቀሱም አጋቾቹ መረጃው ይደርሳቸው ስለነበር እየገረፉ ቤተሰቦቹ አርፈው እንዲቀመጡ እንዲነግራቸው አድርገዋል።

"'ወደ ፖሊስ ከህግ አካል እየሄዱ ነው ተመለሱ በላቸው። ለምንድነው የሚሄዱት? ምን ሊያመጡ ነው? አሁን እጃችን ላይ ነክ። ምን ሊያደርጉ ነው? ከህግ አካልም መረጃ አለን። ከመከላከያ እስከ ፖሊስ ድረስ ምን ሊያደርጉ ገቡ?' አሉኝ። 'ተመለሱ እኔን እኮ ሊገሉኝ ሰኮንድ አልቀራቸውም' እያልኩ ወንድሜን እያወራሁትም ይደበድቡኛል" ብሏል።

ቤተሰቦቹ ያላቸውን ሰብስበው እና ተበድረውም 410 ሺህ ብር ከፍለው እንዲለቀቅ አድርገዋል። "ለእኔ ብቻ ነው 410 ሺህ የተከፈለው። ቤተሰብም ተጨናንቆ ነበር እንገለዋለን እያሉ ስለነበር" ብሏል።

ገንዘቡን ለማሰባሰብ ለሥራ የሚጠቀምባቸውን እንደ ሚዛን ያሉ ቁሳቁሶችን ጨምሮ መጋዘን ውስጥ ያለውን ንብረት ለመሸጥም መገደዱን ይናገራል።

"ከደልጊ እስከ ባህር ዳር ድረስ ያሉ ጓደኞቹ" ያቅማቸውን አዋጥተው ስለረዱኝ ነው የተጠየቀውን ገንዘብ ለመክፈል የተቻለው።

አሁን "ምንም ተስፋ የለኝም" የሚለው መለሰ "ምንም የማስበው የለም አንደኛ ህይወቴን አጥቻለሁ። ሁለተኛ ሠርቼ አገኛለሁ የሚል ዓላማ እስከሌለኝ ድረስ በህይወት ካለሁ ተቀጥሬም ቢሆን እሠራለሁ። ጓደኞቼም ካላቸው ይረዱኛል። ከሌላቸውም ተቀጥሮ መኖር ነው ውሳኔዬ" ሲል ተስፋ በቆረጠ ስሜት ይገልጻል።

መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ይገባዋልም ይላል። "ነገ ተቀጥሬም አንዱ ሥራ ቢያዘኝ እንዲሁ ታግቼ ህይወቴን መገበር እንጂ ለውጥ የለውም። መንግሥት ለሌሎችም ለህብረተሰቡም ለውጥ ቢያመጣ ጥሩ ነው" ሲል ፍላጎቱን አስታውቋል።

መለሰ ከደረሰበት ጉዳት ለማገገም ህክምናው በመከታተል ይገኛል።

ገንዘብ ብቻ ነው የሚፈልጉት

ከመለሰ የኔዓለም ጋር የነበሩት ሌሎች ሁለት ታጋቾችም ተመሳሳይ ምስክርነታቸውን ለቢቢሲ ሰጥተዋል።

ሁለቱም ታጋቾች ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቀም ጠይቀውናል።

ከታጋቾች መካከል አንዱ የሆነው ግለሰብ አግተው ይዘዋቸው የሄዷቸውን ሰዎች እንደማያቋቸው ለቢቢሲ ይገልጻል።

"ማክሰኞ ጭነት ጭነን ከሽንፋ ወደ ገንዳ ውሃ ስንሄድ ነው የያዙን። . . . ሁሉም የጦር መሣሪያ ይዘዋል" ይላል ይህ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ግለሰብ።

ሌላኛው ግለሰብ ደግሞ በተለምዶ ኤፍ ኤስ አር ተብሎ በሚጠራው መኪናቸው ላይ ከተጫነው አኩሪ አተር በተጨማሪ ሁለት ሴቶች እና አራት ወንዶች በድምሩ አራት ሰዎች ተጭነው እንደነበር ተናግሯል።

ከሽንፋ ወደ ገንደ ውሃ እየሄዱ ሳለም 11 ጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች እንዳስቆሟቸው ያስታውሳሉ። በአጋጣሚ ፖሊስ የጫነ መኪና ደርሶ ተኩስ መከፈቱን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በተኩስ ልውውጡ ወቅት ከአጋቾቹ ወገን አንድ እንዲሁም አንድ የፖሊስ አባል ተገደለ።

ሁለቱን ሴቶች ያላቸውን ቀምተው ከመኪናው ጋር ትተዋቸው ሲሄዱ ወንዶቹን ግን ወሰዷቸው።

አጋቾቹ የወሰዷቸው ሰዎች የመኪናው አሽከርካሪ ከእነ ረዳቱ፣ አኩሪ ተሩን የጫነው ግለሰብ እና ሌላ መንገደኛ መሆናቸውንም ግለሰቦቹ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ከአጋቾቹ ጋር አራት ቀናት አብረው መቆየታቸውን የሚናገሩት ግለሰቦቹ መኪናው ላይ ምንም ጉዳት አለማድረሳቸውን ይናገራሉ።

"'ብር አምጡ? ብር ካላመጣችሁ እንገላችኋለን' እያሉ ነው ያቆዩን" ሲል የተናገረው አንደኛው ግለሰብ፣ እነሱ እየተደበደቡ ጓደኞቻቸው ደግሞ ብር እያዋጡ እና ከሰዎች እየለሙኑ ቀናቶች አለፉ።

"በመጨረሻም ብር ተከፍሎ ወጣን። ለእኔ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ብር ነው የተከፈለው። [ግለሰቡ የገንዘቡን መጠን ለቢቢሲ የገለጸ ቢሆንም ማንነቱን ሊያሳውቅ ይችላል በሚል አስቀርተነዋል] ብሩ በአካል ተሂዶ ነው የተሰጣቸው። ሲከፈላቸው ሂዱ አሉን" ይላል።

ገንዘቡ ተከፍሎ ከተለቀቁ በኋላ ጥለውት የሄዱትን መኪና እዚያው እንዳገኙት ገልጾ "አጋቾቹ ብር ብቻ ነው የሚፈልጉት። ብር ነው የሚሉት።. . ." ሲል ይገልጻል።

"ህዝቡ አዋጥቶ እና ለምኖ ነው ገንዘቡን የከፈለልኝ። ብሩን ስንከፍል ሁላችንንም አንድ ላይ ለቀቁን። አምስቶቹ አጋቾች ብሩን ሄደው ሲቀበሉ ቀሪዎቹ ይዘውን ደበቅ ያለ ቦታ ቆዩ። ገንዘቡን መቀበላቸውን ሲያረጋግጡ በስልክ ተነጋግረው ለቀቁን። መንደር አካባቢ ነበር የለቀቁን" ብሏል ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የገለፀ ታጋች።

ከእገታው እንዲለቀቁ መንግስት ምንም እንዳላደረገላቸው ለቢቢሲ ገልጿል።

"እርምጃም እንወስዳለን"

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ደሣለኝ ጣሰው እገታው በተፈጸመበት ወቀት የጸጥታ መዋቅር ደርሶ አንድ የፖሊስ አባል መገደሉን አረጋግጠዋል። "ከአጋቾችችም አንድ ሰው ሞቷል" ሲሉም ያክላሉ።

አጋቾች በቁጥር ከአስር በላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ሰዎቹን ከእገታው ለማስቀረት አለመቻሉን አስታውቀዋል።

ሰዎቹን ከእገታው ለማስለቀቅ ስምሪት ከመደረጉም በላይ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁለት ሰዎች በጥርጣሬ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል ለቢቢሲ።

". . .የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው አካላት ይህን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይታወቃል። እገታ አዲስ አይደለም አልፎ አልፎ በወርም በሁለት ወርም የጸረ ህዝብ አመለካከት ያላቸው ያግታሉ፤ ህይወትም ይጠፋል። ከወራት በኋላ ይሄ ተፈጥሯል። መፈጠር አልነበረበትም አሳዛኝ ነው" ሲሉ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።

"[የእገታው] ዓላማ አንደኛው ግጭት እና ብጥብጥ ለመፈጠር እና ሁለተኛው ደግሞ ሳይሰሩ ለመበልጸግ ስለሚፈልጉ ነው። ምንጊዜም ብር ስጡን ነው የሚሉት" ብለዋል።

ህይወቱ ካለፈው ሰው በተገኘው መረጃ መሠረት እገታው የተፈጸመው ከአካባቢያቸው ውጭ በመጡ ሰዎች መሆኑ ታውቋል ብለዋል።

"ድሮም የባዳ ተልዕኮ ነው አሁንም ይሄው ነው። ይህ እንዳይሆን እየሠራን ነው። እርምጃም እንወስዳለን" ሲሉ አቶ ደሣለኝ ተናግረዋል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ዙሪያ አማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን ሃሳብ ለማካተት ያደረገው ተደጋጋሚ ትረት አልተሳካም።