ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ በፍጹም እንዳታበሳጫት አስጠነቀቀች

ኪም ጆንግ ኡን ከእህታቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን እህት አሜሪካን በጠንካራ ቃላት አስጠነቀቀች፡፡

እጅግ ኃያል ናት የምትባለው የኪም ታናሽ እህት ኪም ዮ ጆንግ፣ አሜሪካ በዚህ ሰዓት አገሯን ሰሜን ኮሪያን የምታበሳጭ ተግባር ከፈጸመች ‹ወዮላት› ብላለች፡፡

እህት ኪም ጆንግ በተለይ ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ መጀመራቸውን ክፉኛ ተችታለች፡፡

የእህት ኪም ጆንግ አስተያየት በብሔራዊ ቴሌቪዥን የተላለፈው አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለመጀመር ደፋ ቀና በምትልበት ሰዓት መሆኑ አነጋጋሪ አድርጎታል፡፡

የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቅርብ ቀናት የደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሶል ይገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ የጉብኝታቸው ዓላማም በአካባቢው እንዴት ዘላቂ ሰላም ማምጣት ይቻላል በሚለው ዙርያ ለመነጋገር ነው፡፡

አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለመነጋገር ፍላጎት ቢኖራትም ፒዮንግ ያንግ ግን ገና ጆ ባይደንን በፕሬዝዳንትነት ስለመቀበሏ እንኳ በይፋ ያለችው ነገር የለም፡፡

ሁለቱ አገሮች በኒውክሊየር እና ባሊስቲክ ሚሳይል ጉዳይ ላይ ሁልጊዜም ጠብ ላይ ናቸው፡፡

የፕሬዝዳንት ኪም እህት ኪም ዮ ጆንግ በዕለታዊው ሮዶንግ ሱሙን ጋዜጣ ላይ እንዲህ ብለዋል፣ ‹ለአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ምክር አለኝ፣ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ጥሩ እንቅልፍ መተኛት ከፈለጉ አገሬን ሰሜን ኮሪያን ከሚያስቆጣ ተግባር ይታቀቡ፡፡›

ከዚህ ንግግር በተጨማሪ የኪም እህት ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ በጋራ የወታደራዊ ልምምድ እያደረጉ መሆናቸው እልም ያለ ጠብ አጫሪነት ነው ብላለች፡፡

‹እኔ ይህን የጠብ አጫሪነት ተግባር ሰሜን ኮሪያን ለመውረር ከመዘጋጀት ለይቼ አላየውም› ስትል ቁጣዋን ገልጻለች፡፡

ኪም ዮ ጆንግ የኃያሉ ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን ታናሽ እህት ስትሆን አሁን በሰሜን ኮሪያ ሁለተኛዋ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡