ቅርስ፡ በአውሮፓ ገበያ በሚሊዮን ፓውንዶች የሚቸበቸቡት አፍሪካዊ የጥበብ ውጤቶች

የቤኒን ነሃስ

የፎቶው ባለመብት, Woolley and Wallis

አንዲት ሴት ለንደን ወደ ሚገኘው ባርክሌይስ ባንክ ታመራለች። ጊዜው በፈረንጆቹ ሚያዚያ 2016 ነበር።

ሴትዮዋ ወደ ባንኩ ያመራችው በባንኩ ጥብቅ ካዝና ውስጥ ለ63 ዓመታት የቆየ ምስጢራዊ ንብረት ፈልጋ ነው።

የባንኩ ሰዎች ወደ ምድር ቤት ይዘዋት ወረዱ።

ሦስት ወንዶች ባንኩ ለደንበኞች ባዘጋጀው ፎቴ ላይ ተቀምጠው አላፊ አግዳሚውን በጥርጣሬ እየተመለከቱ ሴትየዋን ይጠብቃሉ።

ከ20 ደቂቃ ገደማ በኋላ ሴትዮዋ አንድ በአሮጌ ልብስ የተጠቀለለ ዕቃ ይዛ ብቅ አለች።

የተጠቀለለበትን ጨርቅ ስትገልጠው ሁሉም ሰው በአድናቆት አፉን ከፈተ።

ከነሃስ የተሠራ የአንድ ወጣት ሃውልት አፈጠጠባቸው። አንገቱ ላይ ጌጥ አስሯል። ጭንቅላቱ ላይ ደግሞ ቅል መሳይ ነገር ተሸክሟል።

የጭንቅላት ቅርጽ የያዘው ይህ ሐውልት በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበረን ንጉስ ወይም 'ኦባ' የሚወክል ነው።

ፎቴው ላይ ተቀምጠው ከነበሩት ሦስት ወንዶች አንደኛው ደላላ ነው። ላንስ ኤንትዊዝል ይባላል። ሁለቱ ደግሞ አጫራቾች። ሰዎቹ ሐውልቱን ሲመለከቱ ቤኒን ብሮንዝ መሆኑን አልተጠራጠሩም።

ከሦስቱ ወንዶች አንዱ የሆነው ደላላው ላንስ፤ በአፍሪካ ጥንታዊ ንብረቶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጽሓፍት የተደረደሩበት ቤተ-መጽሓፍት አሉት።

ነገር ግን ሰውዬው ናይጄሪያንም ሆነ አህጉረ አፍሪካን በአካል አያውቃትም። ቢሆንም ከእንግሊዝ ሙዚዬም እስከ ፓሪስ፤ አልፎም እስከ ኒው ዮርክ ድረስ በመሄድ የሰበሰባቸውን ንብረቶች ይሸጣል።

ሴትዬዋ ከሐውልቱ ላይ ጨርቁን ስታነሳ የተሰማውን ስሜት በቃላት መግለፅ አልቻለም።

የኧርነስት ልጅ ሐውልቱን በታክሲ ወደ ቤት ይዛ ሄዳ እንድታስቀምጠው ነገራት።

ይህ የቤኒን ብሮንዝ ወደ አውሮፓ የመጣው በ1897 ነው። የብሪታኒያ ወታደሮች የያኔዋ ምዕራብ ቤኒን ግዛት፤ የአሁኗ የናይጄሪያ ኤዶ ግዛትን ቅኝ በገዙ ጊዜ የዘረፉት ነው።

ምንም እንኳን የቤኒን ብሮንዝ ወይም ነሃስ እየተባለ ይጠራ እንጂ የሚሠራው ከነሃስ ብቻ ሳይሆን ከብራስ [መዳብና የብረት ውህድ] ጭምር ነው።

እነዚህ ንብረቶች በእንግሊዝ ሙዚየም ለሕዝብ ይፋ በሆኑ ጊዜ በርካታ ጎብኝዎችን አትርፈዋል።

በቅኝ ግዛት ዘመን በእንግሊዝ ጋዜጣዎች ላይ 'የደም ከተማ' በመባል የምትታወቀው ቤኒን፤ አሁን ጋዜጦቹ እነዚህን ጥንታዊ ንብረቶቿን "አስደናቂ"፣ "አስገራሚ" እያሉ ያሞካሿቸዋል።

ከቤኒን የተዘረፉት እነዚህ ጥንታዊ ንብረቶች አሁንም ድረስ በቅኝ ገዢዎች ቤት ይገኛሉ።

ሌሎች ደግሞ ባለቤት እየቀያየሩ መዳረሻቸው አይታወቅም።

መኖሪያው ኤዶ ግዛት ያደረገው አርቲስት ቮክቶር ኤሂካሜኖር፤ "እነዚህ ነሃሶች "የኛ መረጃዎች፣ ንብረቶች፣ የንጉሦቻችን 'ፎቶግራፎች' ናቸው። ሲዘረፉ ታሪካችንም ነው አብሮ የተዘረፈው"ይላል።

ይሁን እንጂ የእነዚህ ንብረቶች ዋጋ አውሮፓ ውስጥ በጣም የናረ ስለሆነ ብዙዎች ቱጃር ሆነውባቸዋል።

በ1953 ለንደን ውስጥ በተካሄደ ጨረታ አንድ የቤኒን ብሮንዝ 5 ሺህ 500 ዩሮ ዋጋ ነበረው። በ1968 ደግሞ ዋጋው ወደ 21 ሺህ ዩሮ አደጓል።

በ2007 ኒው ዮርክ ውስጥ አንድ የቤኒን ብሮንዝ በ4.7 ዶላር ተሽጧል።

በሞተው ደላላ ልጅ እጅ የሚገኘው የቤኒን ብሮንዝ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያወጣ ላንስ ያውቀዋል። ገዢው ደግሞ ኒው ዮርክ ላይ በነበረው ጨረታ 4.7 ሚሊዮን መዥርጦ የገዛው ማንነቱ የማይታወቅ ግለሰብ እንደሚሆን ጥርጣሬ አልነበረውም።

የአይሁዱ ግለሰብ ሴት ልጅ እጅ የነበረው የቤኒን ብሮንዝም በ10 ሚሊዮን ፓውንድ እንደተሸጠ ላንስ ይናገራል።

ሴትዬዋ በዚህ ገንዘብ ሕይወቷን ቀይራበታለች።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንድ ሰዎች በእጃቸው ያሉ ጥንታዊ ንብረቶችን ለባለቤት ሃገራት እየመለሱ ነው።

መኖሪያውን ዌልስ ያደረገ ዶክተር ከእነዚህ ግለሰቦች አንዱ ነው።

ዶክተሩ ከአያቱ የወረሳቸውን ሁለት የቤኒን ብሮንዝ ሐውልቶችን መልሶ ቤኒን ከተማ ይዞ ሲገባ የጀግና አቀባበል ተደርጎለታል።