ዴሞክራቲክ ኮንጎ የተዘረፉ ቅርሶቿ እንደሚመለሱ ተስፋ ሰንቃለች

የፎቶው ባለመብት, Samir Tounsi via AFP
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዘዳንት፤ በኪንሻሳ አዲስ ብሔራዊ ሙዝየም ይመርቃሉ።
በደቡብ ኮርያ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ተቋም እርዳታ የተገነባውን ሙዝየም ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመት ወስዷል። ባህልና የእለት ከእለት ሕይወትን የሚያሳዩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅርሶችም በሙዝየሙ ይገኛሉ።
የመንግሥት ኃላፊዎች እንዳሉት፤ በቅኝ ግዛት ዘመን ከአገሪቱ የተዘረፉ ቅርሶች ተመልሰው የሙዝየሙ ስብስብ ይሰፋል የሚል ተስፋ አላቸው።
በተለይም አምና በድጋሚ በተከፈተው የቤልጂየሙ 'ሮያል ሙዝየም ፎር ሴንትራል አፍሪካ' ውስጥ የሚገኙ ቅርሶች በዋነኛነት ተጠቅሰዋል።
የቀድሞው የዴሞክራቲክ ኮንጎ መሪ ጆሴፍ ካቢላ፤ በቤልጂየሙ ተቋም ያሉ ቅርሶች እንዲመለሱ እንደሚጠይቁ መናገራቸው ይታወሳል። ሆኖም ይፋዊ ጥያቄ አልቀረበም።
አገሪቱ ነጻነቷን የተቀዳጀችው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1960 ነበር።
ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ገዢዎች የተዘረፉ ቅርሶች ይመለሱ የሚለው ጉዳይ መነጋገሪያ አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል። 2018 ላይ ፈረንሳይ በሺዎች የሚቆጠሩ ቅርሶች ወደ አህጉሪቱ እንዲመለሱ ወስናም ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Arsene Mpiana Monke via AFP
ምዕራባውያን፤ አፍሪካ ውስጥ "የቅርሶች ደህንነት ተጠብቆ የሚቀመጥበት ቦታ እና ፖለቲካዊ መረጋጋት የለም" በሚል ቅርሶችን ለመመለስ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
በዴሞክራቲክ ኮንጎ የተሠራው አዲስ ብሔራዊ ሙዝየም ቀድሞ የነበሩትን ይተካል። የቀድሞዎቹ ሙዝየሞች ለቅርሶች ምቹ አይደለም ይባል ነበር።
በአዲሱ ሙዝየም በሁለት ፎቅ፤ የተለያዩ ቁሳ ቁሶች ተቀምጠዋል። በአገሪቱ በሚገኙት ከመቶ በላይ ብሔሮች የተሠሩ አነስተኛ ቅርጾችና ጭንብሎችን መጥቀስ ይቻላል።
አይሜ ምፔኔ የተባሉ የሥነ ጥበብ መምህር ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የሙዝየሙ ስብስብ ለአገሪቱ ዘመነኛ ሥነ ጥበበኞችን እንደሚያነሳሳ ተስፋ ያደርጋሉ።












