የአፄ ቴዎድሮስን ቁንዳላ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተረከበ

የአፄ ቴዎድሮስን ቁንዳላ የእንግሊዝ ብሔራዊ የጦር ሙዝየም ለኢትዮጵያ መንግሥት አስረክቧል።
በ1868 ዓ.ም ከእንግሊዝ ሃገር ከመጡ በሺህ ከሚቆጠሩ ወታደሮች ጋር መቅደላ ላይ ተዋግተው፤ አፄ ቴዎድሮስ እራሳቸውን ካጠፉ በኋላ ብዙ ንብረትና ቅርሶች ተዘርፈው እንደነበር በታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቧል።
የተዘረፉት ዕቃዎች ለኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ከተነገረ የቆየ ቢሆንም፤ ከእነርሱ መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ በትላንትናው ዕለት በቴዲ አፍሮ ሙዚቃ በታጀበ ደማቅ ዝግጅት በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተረክቧል።
አፄ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ቦታ የነበራቸውና እስካሁንም በጀግንነታቸው የሚጠሩ ናቸው። ከስማቸውና ከአልበገር ባይነት ስሜታቸው በተጨማሪ ደግሞ እስከዛሬ ብዙዎች የሚያነሷቸው በፀጉር አሠራራቸው ጭምር ነው።
በዝግጅቱ ንግግር ያደረጉት የባህልና የቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው የኢትዮጵያን መንግሥትና ሕዝብ በመወከል መጋቢት 11 ቀን 2011 በእንግሊዝ ብሔራዊ የጦር ሙዝየም ተግኘተው የአፄ ቴዎድሮስን ቁንዳላ ተረክበዋል።
"ይሄ የኢትዮጵያ ትልቁና አንዱ ታሪክ ነው። ታሪክን መጠበቅና ታሪክን ማስቀጠል ደግሞ የሃገር ዋና መሠረት ነው" ያሉት ዶ/ር ሂሩት በዚህ ዕለት መገኛታቸው እንዳስደሰታቸው በቦታው ለነበረው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ተናግረዋል።
አክለውም ሥራቸው በዋነኝነት ሕዝቡን ማስተማርና ያለውን ነገር ለሕዝቡ ማሳወቅ እንደመሆኑ "ማንነትን አውቆ እየተደመሩ የሚመጡ ነገሮች ከሌሉ ሃገርን መግለፅ አይቻልም" የሚል አቋማቸውን "የታሪክ ድምር ነው ሃገርን የሚፈጥረው" በማለት ተናግረዋል።
የአፄ ቴዎድሮስ ጀግንነትና እሴት በመጀመሪያ ለኢትዮጵያ "እንደ ጥቁር ሕዝብ ደግሞ ለአፍሪካ ኩራት የሚፈጥር የዓለም ደግሞ ቅርስ ነው" ብለው አንድ ሃገር የእራስን ታሪክ ለማስቀጠል ልፋት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ዶ/ር ሂሩት "ታሪክ የአንድ ሃገር ነው እንጂ የሁሉም ሊሆን አይችልም ስለዚህ ሁሉም የእራሱን ታሪክ መጠበቅ ይኖርበታል" ይላሉ።

በትላንትናው የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከተገኙት ኢትዮጵያዊ ታዳሚዎች መካከል ለ20 ዓመታት በለንደን ነዋሪነቱን ያደረገው ሰለሞን ተረፈ ይገኝበታል። ሰለሞን በግሉ በእንግሊዝ የተለያዩ ከተማዎች እየተዟዟረ በተለያዩ ሙዝየሞች የተቀመጡትን የኢትዮጵያ ቅርሶች ሲጎበኝ እንደኖረ ይናገራል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለይቶ አውቆ ለማስመለስ ከጠየቃቸው ወደ 300 ገደማ ቅርሶች በተጨማሪ ሌሎች ብዙ የማይታወቁና ያልተመዘገቡ ቅርሶች እንዳሉ የሚናገረው ሰለሞን፤ ሃሊፋክስ በተባለ ከተማ በኤዲንብረ ጥንታዊ ቤተ መንግሥት እንዲሁም በሌሎችም ከተሞች ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ ቅርሶችን በማደን ለኢትዮጵያ መንግሥት ሲያሳውቅ ቆይቷል።
በመቅደላው ጦርነት ተሳትፈው የነበሩት የእንግሊዝ ወታደሮች ከስኮትላንድና ከአየርላንድ የተወጣጡ ስለነበሩ እስከ እነዚህ ቦታዎች ድረስ የተወሰዱ የኢትዮጵያ ንብረቶች እንዳሉ ሰለሞን ይናገራል።
"ብዙ ጊዜ እነዚህን የማይታወቁ ቅርሶች ለማስመለስ ከባድ የሚሆነው ለሙዝየሙ በግለሰቦች የተበረከቱ ስጦታዎች በመሆናቸው ነው" የሚለው ሰለሞን በተለያዩ ቦታዎች ያያቸውን ቅርሶች ፎቶግራፍ እንዳያነሳ ለቅርሶቹ ጥበቃ ሲባል ክልክል መሆኑን ይናገራል።
እራሱን የኢትዮጵያ ቅርስ አዳኝ አድርጎ የሰየመው ሰለሞን የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ መመለሱ ደግሞ "የሚያስደስትና ጥሩ ጅማሬ" እንደሆነ ገልጾ "ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጓት አዋቂና የተማሩ የባህል አምባሳደሮች ነው። የእንግሊዞቹን ባህል የሚያውቅ፣ የእነርሱን ቋንቋ እንደነርሱ የሚያውቁ ያስፈልጉናል።"
የአፄ ቴዎድሮስን ቁንዳላ የኢትዮጵያ መንግሥት በእንግሊዝ ይረከብ እንጂ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደሚመጣና የት ሊቀመጥ እንደቻለ ብዙም የታወቀ ነገር የለም።













