ታንዛኒያ ስለጠፉት ፕሬዝዳንት አሉባልታ ያሰራጩ ዜጎቿን አሰረች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የታንዛኒያ ፖሊስ አራት ዜጎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊን በተመለከተ አሉባልታን አስወርተዋል በሚል ነው፡፡
የ61 ዓመቱ አወዛጋቢ ፕሬዝዳንት ከሁለት ሳምንታት በላይ ለሕዝባቸው በይፋ አልታዩም፡፡
ይህንን ተከትሎ የተለያዩ አሉባልታዎች በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች እየወጡ ነው፡፡
አንዳንዶች ፕሬዝዳንቱ ኮሮና ይዟቸው በሕንድ እየታከሙ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ሰውየው ደህና ናቸው፤ በየቀኑ ለሕዝባቸው በቴሌቪዥን የመታየት ግዴታ የለባቸውም፤ ፕሬዝዳንት እንጂ ዜና አንባቢ አይደሉም ይላሉ፡፡
የአሉባልታውን መባዛት ተከትሎ የታንዛኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ካሲም ማጃሊዋ ባለፈው ሳምንት ማጉፉሊ በሰላምና በጤና ሥራቸውን ጠንክረው እየሰሩ ነው ብለው ተናግረው ነበር፡፡
ሆኖም ተቃዋሚዎች ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በፍጹም አልተቀበሉትም፡፡
የተቃዋሚ መሪዎች እንደሚሉት ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ምናልባት በሚሳለቁበት በሽታ በኮቪድ ተይዘው ለሕክምና ከአገር ውጭ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ማጃሊዋ እንደሚሉት ግን እንዲህ ዓይነት አሉባልታ ማስወራት ከጥላቻ የሚመነጭ ነው፡፡
‹ፕሬዝዳንቴን ማጉፉሊን በስልክ አግኝቼዋለሁ፤ ሕዝቤን ሰላም በልልኝ ብሎኛል› ብለዋል አርብ ዕለት፡፡
ትናንት ሰኞ ደግሞ የታንዛኒያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሚአ ሱሉሁ ‹ታንዛናዊያን እባካችሁ ሐሜትና አሉባልታ አትስሙ› ሲሉ ሕዝባቸውን መክረዋል፡፡
‹አንድ ሰው መታመሙ፣ ጉንፋን መያዙ፣ ትኩሳትም ቢኖረው ብርቅ አይደለም፤ አንድነታችን ላይ ማተኮር ያለብን ጊዜ ነው አሁን፤ በጸሎት አንድ መሆን አለብን› ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሚአ፡፡
ሆኖም ምክትል ፕሬዝዳንቷ ይህ አነጋገራቸው ስለ ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ይሁን አይሁን ግልጽ አላደረጉም፡፡
የቢቢሲዋ ዘጋቢያችን ሙኒራ ሁሴን ከዳሬሰላም እንደጻፈጻችው አሉባልታ አውርታችኋል ተብለው የታሰሩት አራቱ ሰዎች ከታንዛኒያ የተለያዩ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎች ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ማፉፉሊ በእርግጥ የት ነው ያሉት የሚለው ጉዳይ በየዕለቱ እያነጋገረ ሲሆን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቱንዱ ሊሱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሁነኛ የወሬ ምንጭ ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ኮቪድ ተይዘው በናይሮቢ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ነግሯቸዋል፡፡
ተቃዋሚው ጨምረው እንዳሉት ጆን ማጉፉሊ አሁን በልብ ሕመም እየተሰቃዩ ሲሆን በሞትና በሕይወት መካከል ናቸው ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ሌላ ስሙን ለደኅንነቱ ሲል የደበቀ የተቃዋሚ መሪም በተመሳሳይ ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ በጠና መታመማቸውን መስማቱን ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡
ማጉፉሊ በኮቪድ ሲሳለቁ የኖሩ መሪ ሲሆኑ ዜጎቻቸው ስለ ኮቪድ እንዳይጨነቁና በጸሎታቸው እንዲበረቱ ይናገሩ ነበር፡፡
ማጉፉሊ በአንድ ወቅት ኮቪድ ውሃ በመታጠን እንዲሁም በባህላዊ መንገድ ቅጠላቅጠልና ሥራሥር በመጠቀም የሚፈወስ ተራ በሽታ ነው ሲሉም ተናግረው ያውቃሉ፡፡












