የሞስኮ ፖሊስ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉባኤን በመክበብ 200 ፖለቲከኞችን በቁጥጥር ስር አዋለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሩሲያ ፖሊስ የተቃዋሚ ፖርቲዎች እያደረጉ ያለውን ጉባኤ ሰብሮ በመግባት 200 ፖለቲከኞችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
ከታሰሩት መካከል ታዋቂ አመራሮች ይገኙበታል ተብሏል።
ለሁለት ቀናት ያህል ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ጉባኤ ገና ከጅማሮው ነው ፖሊስ ያቋረጠው።
ፖሊስ የሞስኮ ሆቴልን ከብቦ ተሳታፊዎቹን በሙሉ በቁጥጥር ስር አውሏል።
ፖሊስ እንደሚለው ፖለቲከኞቹ ስብሰባ በማካሄድ የኮሮናቫይረስ መመሪያዎችን ጥሰዋል እንዲሁም ይህንን ጉባኤ ያዘጋጀው "የማይፈለግ ድርጅት" ነው ብሏል።
አገሪቷ የምታደርገው ምርጫ እየተቃረበ በመጣበት ወቅት ባለስልጣናቱ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ የሚያደርጉት ጫና ከፍተኛ ነው ተብሏል።
ባለፈው ወር ዋነኛ ተቃዋሚና ቭላድሚር ፑቲንን በሰላ ትችቱ የሚታወቀው አሌክሴ ናቫልኒ ለእስር ተዳርጓል።
ተመርዞ የነርቭ ጉዳት ያጋጠመው አሌክሴ ህክምና አድርጎ ጀርመን ከተመለሰ በኋላ ነው ለእስር የተዳረገው።
ባለስልጣናቱ በይደር የቆየውን የፍርድ ቤት እስር ውሳኔ ጥሷል ተብሏል።
አሌክሴ መርዘውኛል የሚላቸው የክሬምሊን ቤተ መንግሥት ባለስልጣንን ነው።
በአጠቃላይ በሩሲያ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በዚህ ሞስኮ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ነበር። የዚህ ጉባኤ ዋነኛ አላማ በመጪው መስከረም ላይ አገሪቷ የምታደርገው ብሄራዊ ምርጫ ላይ ያሉ ስትራቴጂዎችን ለመወያየት ነበር የተዘጋጀው።
የአገሪቱ ቴሌቪዥን እንዳሳየው የጉባኤው ተሳታፊዎች በፖሊስ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ነው።
ፖሊስ "በርካታ ተሳታፊ ፖለቲከኞች ጭምብል አላጠለቁም" ያለ ሲሆን እንዲሁም ሌሎች የኮሮናቫይረስ መመሪያዎችንም ጥሰዋል ይላል።
ጉባኤውን አዘጋጅቷል የተባለውና "ያልተፈለገ ድርጅት" ተብሎ የተጠራው ኦፕን ሩሲያ እንደሆነ ፖሊስ አስታውቋል።
ኦፕን ሩሲያ የተቋቋመው የሩሲያ ዋነኛ ተቃዋሚ በሚባሉት ሚክሃይል ኮዶሮኮቭስኪ በእንግሊዝ ውስጥ ነው።
ሚክሃይል ኮዶሮኮቭስኪ በእስር ለአስር አመታት የቆዩ ሲሆን ጠበቆቻቸው በፈጠራ ክስ ነው የታሰሩት ብለዋል። ፖለቲከኛው ከእስር በኋላ ውጭ አገር በስደት መኖር ጀምረዋል።
የሩሲያ ባለስልጣናት የውጭ አገር ድርጅቶች ሆነው በፖለቲካ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች በአገሪቱ መንቀሳቀስን ያግዳል። በአገሪቱም ውስጥ "የማይፈለጉ" ከተባሉ ድርጅቶች አንዱ ነው።
በጉባኤው ተሳታፊ የሆኑት አንደኛው የተቃዋሚ መሪ አንድሬይ ፒቮቫሮቭ በበኩላቸው ዩናይትድ ዲሞክራትስ በሚባል ድርጅት ጉባኤው እንደተካሄደ ተናግረዋል።
የፖሊስ ከበባ "እኛን ማስፈራራት" ላይ ያነጣጠረ ነው ይላሉ።












