ከስልጣን በኃይል የተወገዱት የሚየንማር አመራሮች 'አብዮት' ለማስነሳት ቃል ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከስልጣናቸው በኃይል የተወገዱት የሚየንማር አመራሮች በወታደራዊው አመራር ላይ አብዮት ለማስነሳት ከሰሞኑ ቃል ገብተዋል።
እነዚህ አመራሮች ተደብቀው ነው የሚገኙት ተብሏል።
በአገሪቱ ላይ መፈንቅለ መንግሥት መነሳቱን ተከትሎ በዝምታ ላይ የነበሩት የቀድሞ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ማህን ዊን ክሃይንግ ታን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ የሆነ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
"በአገራችን ታሪክ ውስጥ እንዲህ አይነት የጨለመ ወቅት አጋጥሞን አያውቅም። በቅርቡ ግን መንጋቱ አይቀርም" ብለዋል።
ማህን መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በፌስቡክ ሲሆን "ሁሉንም ብሄሮች ያካተተ ፌደራላዊ ዲሞክራሲ ለመመስረትና ለዘመናትም ያህል በአምባገነንነት የጨቆነን ስርዓት ለመገርሰስ ወቅቱ አሁን ነው። ሁላችንም ተባብረን አብዮት ልናስነሳ ይገባል" ብለዋል።
አክለውም "ምንም እንኳን ልዩነቶች ቢኖሩንም እነሱን አቻችለን፤ ይህንን አምባገነናዊ ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቃ ልንለው ይገባል። አብዮት እናስነሳለን" በማለት ተናግረዋል።
የቀድሞው ሚኒስትር ከተደበቁበት ሆነው ስልጣን በኃይል የጨበጠውን ወታደራዊ አገዛዝ የተቃወሙ የፓርላማ አባላት ቡድንን ይመራሉ።
መፈንቅለ መንግሥት ከተነሳ ጀምሮ በተቃውሞ እየተናጠች ባለችው ሚየንማር በትናንትናውም ዕለት 12 ሰዎች ተገድለውባታል።
በቀድሞ ስሟ በርማ ተብላ የምትጠራው ሚየንማር ከወር በፊት በተነሳ መፈንቅለ መንግሥት የሲቪል አመራር የነበሩትን አንግ ሳን ሱ ቺን ከስልጣን ከማስወገድ በተጨማሪ ለእስር ዳርጓቸዋል።
አንግ ሳን ሱ ቺ ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ (ኤንኤልዲ) የተባለው የገዢው ፓርቲ መሪ ናቸው።
ሚየንማር ባደረገችው ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት ኤንኤልዲ ስልጣን መቆጣጠር ቢችልም ወታደራዊው አገዛዝ ምርጫው ተጭበርብሯል ይላል።
ወታደራዊው አገዛዝ የተወሰኑ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ቢያውልም ማምለጥ የቻሉ የፓርላማ አባላት አዲስ የአመራር ቡድን አቋቁመዋል።
የዚህ ቡድን መሪ ማህን ዊን ክሃይግ ታህን ሲሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃም የሚየንማር ትክክለኛ መንግሥት ነን በማለት እውቅና ለማግኘት እየጣሩ ነው።












