የኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማኅበርን ማቋቋም ለምን አስፈለገ?

የኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማህበር መስራቾች በከፊል

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Youth Entrepreneur Association

ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ ከስድስት መቶ በላይ አባላት ያሉት እና ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን የያዘ ማኅበር መመስረቱን መሥራች አባላቱ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የሥራ ፈጣሪዎች ማኅበር መስራችና ፕሬዝዳንት የሆነችው ሳሚያ አብዱል ቃድር ማኅበሩ በኢትዮጵያ ደረጃ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጻለች።

ሳሚያ ኤም ቪው አጠቃላይ የትምህርት አማካሪ እና የባለሙያ ድጋፍ ሰጪ መስራችና ፕሬዝዳንት ስትሆን ተቋሙ የኢትዮጵያን ትምህርት በአዎንታዊ አስተሳሰብ ለማዘመን እንደሚሰራ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ከመስራች አባላቱ መካከል አንዱ የሆነው ቀረመንዝ ካሳዬም በበኩሉ ከስድስት በላይ በስሙ የተመዘገቡ የፈጠራ ሥራዎች ያሉት መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።

ቀረመንዝ የሥራ ፈጣሪዎች በተለያዩ ስፍራዎች በየግላቸው እየሮጡ እንደሚገኙ አስታውሶ፣ ለየብቻ መሮጣቸው ያስገኘው ይህ ነው የሚባል ውጤት አለመኖሩን በማንሳት ማኅበር ማቋቋሙ ጠቃሚ እንደሆነ ይናገራል።

ይህ ከስድስት መቶ በላይ የተመዘገቡ አባላት መያዙ የተገለፀው ማኅበርን መመስረት የፈለጉበትን ምከንያት ሲያስረዱም አስፈላጊው ክትትል እና እገዛ ቢደረግላቸው ጥቅማቸው ለሌሎች የሚተርፉ የሥራ ሃሳብ ፈጣሪ ወጣቶችን መደገፍ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ይላል።

"ዓለም አሁን ለደረሰችበት ደረጃ የበቃቸው በሥራ ፈጣሪዎቿ ነው" የሚሉት ሳሚያ እና ቀረመንዝ፣ ሕይወትን የሚያቀሉና የሚያቀላጥፉ ፈጠራዎች ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ተገቢው ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም ተሞክሮን በመጥቀስ ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ የሥራ ፈጣሪዎች ላይ ተግዳሮቶች እንደሚበዙ የምትናገረው የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሳሚያ፣ ከአሁን በኋላ የሚመጡ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥማቸው በማሰብ ማኅበሩ መቋቋሙን ገልጻለች።

በትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በሌሎች ኢትዮጵያን ዕድገት በሚያሳልጡ ዘርፎች ሁሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች በሥራ ፈጠራ እና በሥራ ፈጠራ ሃሳብ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ የሚያመለክቱት ወጣቶቹ፤ ነገር ግን ያላቸውን ርዕይ ወደ ተግባር ላይ ለመለወጥ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚገጥማቸው ይናገራሉ።

በመላ አገሪቱ የሚገኙ የሥራ ፈጣሪዎች በአገር ውስጥ እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ካሉ ባለሙያዎች ጋር ማስተሳሰር፣ ሃብቶችን ማሰባሰብ እና የክህሎት ሥልጠናን ለአባላቱ መሥጠት ከማኅበሩ አላማዎች መካከል ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የሥራ ፈጣሪዎች ወደ ሥራ ፈጣራ ኮሚሽንም ሆነ ወደ ኢኖቬሽን ሚኒስቴር በተበታተነ መልኩ በመሄድ ድጋፍና እገዛ እንደሚጠይቁና ይህ ግን ለተቋማቱም ሆነ ለሥራ ፈጣሪዎቹ አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራሉ።

ስለዚህ ማኅበራቸው መመስረቱ በጋራ በመሆን የሚያስፈልጓቸውን ጉዳዮች ለመጠየቅ እንዲሁም የሥራ ፈጣሪዎችን በተገቢው መልኩ ለማገዝ ይረዳል ይላሉ።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት የሆነችው ሳሚያ አብዱል ቃድር፣ ይህ ማኅበር መቋቋሙ የሥራ ፈጣሪዎችን ውጣ ውረድ በግማሽ እንደሚቀንሰው በመግለጽ፣ ከተለያየ የመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት እንደሚፈልጉ ትናግራለች።

የኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማህበር መስራች እና ፕሬዝዳንት

የፎቶው ባለመብት, Samia Abdulkadir

እነዚህ ወጣቶች እንቅፋት በገጠማቸው ቁጥር እነርሱም ሆነ አገር ተገቢውን ጥቅምና ግልጋሎት ከማግኘት እንደሚሰናከሉ የምታስረዳው ፕሬዝዳንቷ፣ ይህ ማኅበር ሥራ ፈጣሪዎች እርስ በእርሳቸው መደጋገፍ እንዲችሉ በማሰብ የተመሰረተ ነው ብላለች።

በርካታ ወጣቶች በመደበኛው ትምህርት ውስጥ የሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ሳይሆን የተቀጣሪነትን አስተሳሰብ እንዲይዙ ተደርገው መሰልጠናቸውን በማስታወስም፣ ማህበሩ ለሥራ ፈጣሪ አባላቱ የክህሎት እና ራስን የማነጽ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥም ተናግራለች።

ሳሚያ፣ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ትክክለኛ ቀጥተኛ እና ጠቃሚ የሆነ መረጃ በማግኘት ረገድ ክፍተት እንዳለባቸው ጠቅሳ፣ ማኅበራቸው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያለውን ክፍተት ለመድፈን እንደሚሰራም ገልጻለች።

በተጨማሪም ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች፣ ስለ አዳዲስ ሕጎች፣ የሥራ ፈጠራቸውን የት ይዘው መሄድ እንዳለባቸው፣ ለተለያዩ ጉዳዮቻቸው ማሟላት ያለባቸውን መሥፈርቶችን በሚመለከት ማኅበራቸው እገዛ ለማድረግ እና መረጃ ለማቅረብ ይሰራል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በተመሳሳይ መስክ በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎችን አሉ የሚሉት ሳሚያ እና ቀረመንዝ፣ ማኅበራቸው እነዚህን ባለሙያዎች በማስተሳሰር እርስ በእርስ የሚደጋገፉበት እና መረጃ የሚለዋወጡበትን መንገድ እንደሚያመቻች ይናገራሉ።

የሥራ ፈጣሪዎችን ከባለሀብቶች፣ ከመንግሥት እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ማስተሳሰር ሌላ ዓላማቸው መሆኑንም ሳሚያ ገልጸለች።

ወጣቶች ያላቸውን የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ዋነኛ እንቅፋት ከሆኑት መካከል ገንዘብ አንዱ መሆኑን ያነሳችው ሳሚያ፤ ለእነዚህ ወጣቶች የገንዘብ ምንጮችን ማፈላለግ እና ማገናኘት ከተመሰረቱባቸው እና ከሚሰሩባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።

የሥራ ፈጣሪዎች በተለያዩ ፖሊሲዎች እንዲታገዙ እና እንዲበረታቱ ለማድረግ ፖሊሲዎችን እና ደንቦች አመቺ ለማድረግ እንደሚሰሩም ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማኅበር በሁሉም ክልሎች ቢሮዎችን ለመክፈት እቅድ መያዙን የምትናገረው ሳሚያ፣ በተለያዩ ቋንቋዎችም በመገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን ለማድረስ መዘጋጀታቸውን ገልጻለች።