ትግራይ፡ አሜሪካ ትግራይ ውስጥ "የዘር ማፅዳት ወንጀል" ተፈጽሟል አለች

የፎቶው ባለመብት, Pool
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትግራይ ሕዝብ "የዘር ማፅዳት ወንጀል" (ኤትኒክ ክሊንሲንግ) መፈጸሙን ተናገሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በትናንትናው ዕለት ለአገሪቱ ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ቀርበው ማብራሪያ ባቀረቡበት ወቅት ትግራይ ውስጥ እየተፈፀመ ነው ያሉትን "የዘር ማፅዳት ወንጀል ከማውገዝ" በተጨማሪ "ሙሉ ተጠያቂነት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።
በክልሉ እየደረሰ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ግድያዎች ላይ ተዓማኒ መረጃዎች አሉ ያሉት አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን እንዲያስቆም ጠይቀዋል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹን ከማስቆም በተጨማሪ የጎረቤት አገር ኤርትራ ወታደሮችና የአጎራባቹ ክልል አማራ ሚሊሺያ እንዲወጡም ጠይቀዋል።
"በትግራይ ክልል ውስጥ ከኤርትራ የመጡ የውጭ አገር ሠራዊት አባላት አሉ እንዲሁም ከአጎራባቹ ክልል አማራ ክልል የገቡ ወታደሮች አሉ። እነዚህ ኃይሎች ሊወጡ ይገባል" በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህ ቀደም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተጠቀሱት ወታደሮች ከትግራይ ክልል እንዲወጡና ተኩስ አቁም እንዲደረግ በመጠየቅ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በሰጠው ምላሽ "እንደ ሉዓላዊት አገር ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ኃላፊነት ነው" ያለ ሲሆን፤ "ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የትኛውንም የጸጥታ መዋቅር ማሰማራት የመንግሥት ኃላፊነት ነው" ብሏል በመግለጫው።
በትናንትናው ዕለት ከምክር ቤቱ ኮሚቴ በክልሉ "የሰላም አስከባሪዎች ሊሰማሩ ይችላሉ" ተብሎ በቀረበላቸውም ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአካባቢው ሊኖር የሚገባ የፀጥታ ኃይል ኃይል ምን መምሰል እንደሚገባው አስረድተዋል።
"በአካባቢው መሰማራት ያለበት የፀጥታ ኃይል የትግራይ ነዋሪዎችን ሰብዓዊ መብት የማይጥስ መሆን አለበት። ወይም በምዕራብ ትግራይ እንዳየነው የዘር ማፅዳት ወንጀል የማይፈፅም ሊሆን ይገባዋል። ይህም ሊቆም ይገባል" ብለዋል።
"በአካባቢው የተፈፀሙትን ጥሰቶች ለማጣራት ነፃ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ" ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በተጨማሪም "አገሪቱ በፖለቲካው ወደፊት እንድትራመድ ለማስቻል የእርቅ ሂደትን አስፈላጊነትም" ጠቅሰዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር በተደጋጋሚ በስልክ መወያየታቸውን የጠቀሱት ብሊንከን "ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በህወሓት ላይ ያላቸውን ስጋት እጋራለሁ፤ ነገር ግን በትግራይ ላይ እየተፈፀመ ያለው ነገር ተቀባይነት የለውም ሊቀየር ይገባል" ብለዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት አስተያየት ባይሰጥም ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ "ተፈፅመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር እርምጃዎችን መንግሥታቸው መውሰዱን" ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል።
በመግለጫቸው ምርመራ ለማካሄድም አስፈላጊ ናቸው ከተባሉ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አምነስቲና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ጨምሮ እንዲሁም የአይን እማኞች የኤርትራ ሠራዊት በክልሉ ላይ የዘፈቀደ ግድያዎችን፣ መደፈሮችንና ሌሎች ጥሰቶችን እያካሄደ መሆኑን ይናገራሉ ።
ይህንን ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የኤርትራ መንግሥት አይቀበሉትም።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ሚሼል ባሽሌት ባለፈው ሳምንት በክልሉ እየተፈፀመ ያለው ጥሰት "የጦር ወንጀልና በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል" ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል መናገራቸው የሚታወስ ነው።
በዚህም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉትንና እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ሪፖርት የተደረጉ የጅምላ ግድያዎችን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ወሲባዊ ጥቃቶችን ለመመርመር እንዲችል ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቋል።
ከሰሞኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከትግራይ ክልል ግጭት ጋር በተያያዘ የተነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ግድያዎችን በተመለከተም መንግሥት ከፌደራል ፖሊስ፣ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመጣመር ይመረምራል ብለዋል።
ጨምረውም የእነዚህን አካላት ምርመራ መሰረት በማድረግም መንግሥታቸው በድርጊቱ ውስጥ እጃቸው ያለበትን አካላት ወደ ፍትህ እንደሚያቀርብ አፅንኦት ሰጥተው፤ በምርመራው ላይ ተጨማሪ እርዳታ ካስፈለገ መንግሥት የውጭ አካል ሊጋብዝ እንደሚችል ጠቆም አድርገዋል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት በመፈፀሙ መንግሥት "ሕግ የማስከበር" ወታደራዊ ዘመቻን ማካሄዱን ገልጿል።
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን ቢገልጽም በአንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወታደራዊ ግጭቶች እንዳሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከፍተኛ ኮሚሽነሯም በአሁኑ ወቅት በማዕከላዊ ትግራይ ጦርነቱ መቀጠሉንም መረጃ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።











