ተቃዋሚዎች የአርጀንቲናው ፕሬዝደንት ያሉበትን መኪና መስታወት ሰባበሩ

የአርጀንቲና ፕሬዚዳንት መኪና

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በርካታ ተቃዋሚዎች የአርጀንቲው ፕሬዝደንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝን የያዘችውን መኪና ማጥቃታቸው ተሰማ።

ይህ የሆነው ፓታጎኒያ በተሰኘችው ግዛት ሲሆን ፕሬዝደንቱ 'ሚኒባስ' ውስጥ ነበሩ ተብሏል።

በደቡባዊቷ የአርጀንቲና ክፍለ ግዛት ቹቡት በሚገኝ አንድ የሕብረተሰብ ማዕከል ውስጥ የነበሩት ፕሬዝደንቱ በተቃዋሚዎች ተከበው ድንጋይ ተወርውሮባቸዋል።

ተቀዋሚዎቹ የፕሬዝደንቱ መኪና በመክበብ ተሽከርካሪዋ ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

ፕሬዝደንቱ ወደ ሥፍራው ያቀኑት በአካባቢው የተነሳውን ሰደድ እሣት ተከትሎ አንድ ሰው መሞቱን በርካቶች መጎዳታቸውን በማስመልከት ነው።

ነገር ግን ተቃውሞው በቹቡት ግዛት ሊካሄድ ነው የተባለውን የማዕድን ቁፋሮ የተመለከተ ነው።

ተቃዋሚዎቹ መንግሥት ለትላልቅ ማዕድን ቆፋሪ ድርጅቶች ፈቃድ ለመስጠት ረቂቅ ማውጣቱን በመቃወም ድምፃቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

አካባቢው ወርቅ፣ ብርና ዩራኒየምን በመሳሰሉ ማዕድናት የበለፀገ ነው ሲል ክላሪን ጋዜጣ ዘግቧል።

በሥፍራው የነበረውን ግርግር የሚያሳዩ ተንቃሳቃሽ ምስሎች ላይ ፕሬዝደንቱ ከማሕበረሰብ ማዕከሉ ወጥተው ወደ መኪናቸው ሲሄዱ ተቃዋሚዎች የማዕከሉ በር ላይ ተኮልኩለው ይታያሉ።

ከዚያ ተቃዋሚዎቹ ፕሬዝደንቱን ተከትለው የተሳፉበትን ሚኒባስ ሲደበድቡና እንዳይንቀሳቀስ ሲያግዱት ተስተውሏል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች የመኪናዋ መስታወት ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ ነበር።

ምንም እንኳ ፕሬዝደንቱ የነበሩባት መኪና ሕዝቡን ተሻግራ ማለፈው ብትችልም በርካታ መስኮቶች ተሰባብረዋል።

በአርጀንቲናዋ ፓታጎኒያ ግዛት የተነሳው ሰደድ እሣት በርካቶች ቀያቸውን ጥለው እንዲወጡ አስገድዷል።

በሰደዱ እሣቱ ምክንያት እስካሁን ድረስ ቢያንስ 200 ቤቶች ተቃጥለዋል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸውና የውሃ አቅርቦት ማግኘት ያልቻሉ በርካቶች ናቸውም ተብሏል።

ምንም እንኳ የሰደድ እሣቱ መንስዔ ባይታወቅም የሃገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ይላል።