በቡድን ተደፍራ የተገደለችውን ሴት ታሪክ ለመዘገብ በመሞከሩ የታሰረው ሕንዳዊ ጋዜጠኛ

ሲዲሂኬ ካፓን ይለቀቅ የሚል ፖስተር

የፎቶው ባለመብት, Shaheen Abdulla

የምስሉ መግለጫ, ሲዲሂኬ ካፓን ይለቀቅ የሚል ፖስተር

በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር ሲገባ በሰሜን ሕንድ ወደምትገኘው ፕራዴሽ ግዛት አቀናሁ።

ወደ ግዛቲቷ የሄድኩበት ዋነኛ ምክንያትም "ሃትራስ" የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ተደፍራ የተገደለች ሴትን ጉዳይ በተመለከተ በጥልቀት ዘገባ ለመስራት ነው።

ከቀናት በፊት የ19 ዓመት ሴት ከላይኛው መደብ በሆኑ አራት ወንዶች በደቦ ተደፍራ ተገድላ ነበር።

መደፈሩም ሆነ ግድያው የተፈፀመው ቅንጦት በተሞላበት ሃትራስ በሚባል ሰፈር ነው።

ወጣቷ ተደፍራ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሏ እንዲሁም ያለ ቤተሰቦቿ ፈቃድ በሕንድ ባህል እንደሚደረገው አስከሬኗ ተቃጥሎ አመዷ እንዲበተን መደረጉ በዓለም ላይ ባሉ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል።

አካባቢው ደርሼ በሐዘን የተሞሉ ቤተሰቦቿን አገኘሁ። ቤተሰቦቿ፣ ዘመዶቿም ሆነ ጎረቤቶቿ ስለእሷ የሚሉት ነገር ቢኖር ቆንጆ፣ ትንሽ አይናፋርና ረዥም ጥቁር ፀጉር ያላት መሆኑን ነው።

በተደፈረችበት ወቅት አካሏ ላይ ስለደረሰባት ድብደባ ፖሊስ ከሞተች በኋላ እንዴት ያለምንም ማጣራት እንድትቀበር እንደፈለገና መንግሥት ጉዳዩን ለምን መሸፋፍን እንደፈለገ አስረዱኝ።

እኔ አካባቢው በደረስኩበት በዚያኑ ጥዋት ሲዲሂኬ ካፓን የተባለ በማላያላም ቋንቋ የሚሰራ የ41 ዓመት ጋዜጠኛ ወደ አካባቢው እየመጣ ነበር።

ለዘጠኝ ዓመታት ያህል መኖሪያውን በዋና መዲናዋ ዴልሂ ያደረገው ሲዲሂኬ ብሁልጋርሂ መንደር ለመምጣት ያሰበው እንደኔው ተደፍራ የተገደለችውን ሴት ታሪክ ለመዘገብ ነበር።

ጉዞው ግን እንደኔው የተቃና አልነበረም።

ሃትራስ የሚባለው ሰፈር አካባቢ ለመድረስ 42 ኪሎ ሜትር ሲቀረው እሱና ሦስት ሌሎች ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ። በወቅቱም ወደ ስፍራው ለማምራት በመኪናው ውስጥ ነበሩ። ባለፈው ሳምንትም በእስር ላይ 150ኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

በቡድን ተደፍራ የተገደለችው ግለሰብ ቤተሰቦች
የምስሉ መግለጫ, በቡድን ተደፍራ የተገደለችው ግለሰብ ቤተሰቦች

ሲዲሂኬ ካፓን በቁጥጥር በዋለበት በዚያው ምሽት በዱላ ተደብድቧል፣ ፖሊሶች በጥፊ በተደጋጋሚ አጩለውታል እንዲሁም ሙሉ ሌሊቱን በሙሉ ሳይተኛ ጥያቄ ሲጠየቅ እንደነበር ቤተሰቦቹና ጠበቆቹ ይናገራሉ።

ጋዜጠኛው የስኳር ህመምተኛ ቢሆንም መድኃኒቱን እንዳይወስድ ተከልክሏል።

ፖሊስ በበኩሉ ጋዜጠኛው ላይ የተባለው ነገር አልተፈፀመም ይላል።

ፖሊስ እንደሚለው ጋዜጠኛው በቁጥጥር የዋለበት ዋና ምክንያት ወደ ሃትራስ በመሄድ በተለያዩ የማኅበረሰቡ መደቦች መካከል አመፅ ለማነሳሳት አሲሯል በማለት ሲሆን ፖሊስ ሁእርምጃውን ሕግ ማስከበር እንደሆነ አስታውቋል።

መኪና ውስጥ አብረውት የነበሩ ሦስት ግለሰቦችም እንዲሁ በተመሳሳይ ተወንጅለዋል።

ከሲዲሂኬ ጋር አብረው ሲጓዙ የነበሩት ሦስት ግለሰቦች በኬራላ ግዛት ተቀማጭነቱን ያደረገው ፖፑላር ፍሮንት ኦፍ ኢንዲያ (ፒኤፍአይ) ተብሎ ከሚታወቀው ፅንፈኛ የሙስሊም እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት አለው የሚባል ድርጅት አባል ናቸው ተብለዋል።

የኡታር ፕራዴሽ ግዛት ድርጅቱ እንዲታገድ ጥሪ አቅርቧል።

ፖሊስ ሲዲሂኬ የተዘጋ ጋዜጣ ላይ እሰራለሁ በማለት አጭበርብሯል በማለት የከሰሰው ሲሆን በዋነኝነት ግን የፒኤፍአይ አባል ነው ይላል።

የኬራላ የጋዜጠኞች ማኅበር፣ የጋዜጠኛው ጠበቃ እንዲሁም ፒኤፍአይ በፖሊስ ውንጀላ አይስማሙም።

ሲዲሂኬ በአመራር ላይ ያለበት የጋዜጠኞች ማኅበር በበኩሉ የኡታር ፕራዴሽ ፖሊስ "ፍፁም ሐሰተኛ መግለጫ" በማውጣት ከመወንጀሉም በተጨማሪ የጋዜጠኛውን እስር "ሕገ ወጥ ነው" ብሎታል።

ማኅበሩ እንደሚለው ሲዲሂኬ ወደ ሃትራስ ያመራው ለዘገባ እንደሆነና ብቸኛ ሥራውም ጋዜጠኝነት እንደሆነ ተናግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ከእስር እንዲለቀቅም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የተቃውሞ ፊርማ አስገብቷል።

ሲዲሂኬ የሚሰራበት አዝኢምኡካም የተባለው ሚዲያም በበኩሉ ጋዜጠኛው ሠራተኛቸው እንደሆነና ወደ ሃትራስም ያቀናው ለዘገባ ተመድቦ እንደሆነ በመግለጫው አስታውቋል።

የሲዲሂኬ ባለቤት ራይሃናት ከልጆቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Shaheen Abdulla

የምስሉ መግለጫ, የሲዲሂኬ ባለቤት ራይሃናት ከልጆቿ ጋር

ጋዜጠኛ ሲዲሂኬን እንዲሁም የጋዜጠኞች ማኅበሩን የወከሉት ጠበቃ ዊልስ ማቲውስ ደንበኛቸው ቀለል ባለ ወንጀል መከሰሱንና ዋስትና የማያስከለክል መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ነገር ግን ግን ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር ከዋለ ከሁለት ቀናት በኋላ ሲዲሂኬ 'አንሎውፉል አክቲቪቲስ ፕሪቨንሺን አክት' ተብሎ በሚጠራው የፀረ-ሽብር ወንጀል ተከሰሰ፤ በዚህም በዋስ መውጣት አይችልም።

ጠበቃው በበኩላቸው ደንበኛቸው "መቶ በመቶ ገለልተኛና ነፃ ጋዜጠኛ ነው" ይላሉ።

አክለውም "ከግለሰቦች ጋር በአንድ መኪና ውስጥ መሳፈር ጥፋተኛ ሊያስብልህ አይገባም" በማለትም ይከራከራሉ።

"አንድ ጋዜጠኛ በተለያየ የህይወት አቅጣጫ ላይ ያሉ ሰዎችን ያገኛል። ይህም በወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦችንም ሊያካት ይችላል። የተወነጀሉ ሰዎች ጋር አንድ ላይ መገኘት ሊያሳስር አይገባም" ይላሉ ጠበቃ ዊልስ ማቲውስ።

ጋዜጠኛው ከታሰረ ከሳምንታት በኋላ ማንኛውንም ሰው እንዳያገኝ መከልከሉንም የፍርድ ቤት መረጃ ያሳያል።

ቤተሰቦቹን ጋር መደወል የቻለው ከታሰረ ከ29 ቀናት በኋላ ነበር። ባለቤቱንም ከሰላሳ ስድስት ቀናት በኋላ ነው በስልክ ማናገር የተፈቀደለት።

ጠበቃው ዊልስ ማቲውስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተቃውሞ ፊርማ ካስገቡና ጋዜጠኛው ከታሰረ ከ47 ቀናት በኋላ ነው ማናገር የቻሉት።

የሲዲሂኬ ባለቤት ራይሃናት ባለቤቷ በስልክ ደውሎ እስኪያዋራት ድረስ በህይወት መኖሩን እርግጠኛ እንዳልነበረች በስልክ ተናግራለች።

በቅርቡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋዜጠኛው በጠና የታመሙት የ90 አመት እናቱን እንዲጠይቅ በማለት ለአምስት ቀናት ያህል በዋስ እንዲወጣ ፈቅዶለታል።

በነዚህ ቀናትም ከኡታር ፕራዴሽ የመጡ ስድስት ፖሊሶችና በበርካታ የፌደራል ፖሊሶች ጥበቃ ስር ነበር።

የሲዲሂኬ እናት

የፎቶው ባለመብት, Shaheen Abdulla

የምስሉ መግለጫ, የሲዲሂኬ እናት

የጋዜጠኛው የእናቱ ጉብኝት በፍራቻ የተሞላ እንደነበር ባለቤቱ ራይሃናት ትናገራለች።

"የእናቱ የጤና ማሽቆልቆልና የእኛም የገንዘብ ሁኔታና የሦስቱ ልጆቹ የወደፊቱ እጣ ፈንታ በጣም ያስጨንቀዋል" ብላለች።

ባለቤቷ ምንም ስህተት እንዳልሰራና ኢላማ የሆነውም ሙስሊም በመሆኑ እንደሆነ ትናገራለች።

እንደ ራይሃናት ከሆነ ፖሊሶች በተደጋጋሚ ባለቤቷን የበሬ ሥጋ በልቶ እንደሆነ ጠይቀውታል።

በሂንዱ እምነት ተከታዮች ዘንድ ላምና በሬ እንደ ቅዱስ እንስሳ ተደርገው የሚታዩ ሲሆን በቅርብ ዓመታትም ሙስሊሞች የበሬ ሥጋ በመብላታቸው እንዲሁም በማጓጓዛቸው ኢላማ ሆነዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቷ ውስጥ አወዛጋቢ የሚባሉት የእስልምና እምነት ሰባኪ የሆኑት ዶክተር ዛኪር ናይክ ጋር ምን ያህል ጊዜ ተገናኝቶ እንደሆነም በተደጋጋሚ በፖሊሶች መጠየቁን ባለቤቱ ትናገራለች።

ሰባኪው ዶክተር ዛኪር ናይክ መኖሪያቸውን በግዞት በማሌዥያ ያደረጉ ሲሆን በጥላቻ ንግግርና ሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ተከሰዋል። ሰባኪው ግን ይህንን አይቀበሉትም።

ጋዜጠኛው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዳሊት ከሚባሉት ዝቅተኛ የደረጃ መደብ ላይ ከሚቀመጡት ማኅበረሰብ ጋር ለምን ጥብቅ ግንኙነት እንዳለቸው በተደጋጋሚ ፖሊሶች መጠየቃቸውንም ባለቤቱ ጠቅሳለች።

ዳሊት የሚባሉት ማኅበረሰብ በቀድሞው የማይነኩ (አንተቼብልስ) ተብለው የሚጠሩ ናቸው።

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ ከፍተኛ ጠበቃ የሆነው አብሂላሽ ኤምአር እንደነገረኝ ከሆነ "የሲዲሂኬ ካፓን እስር ከፀረ- እስልምና ጋር የተገናኘ ነው የሚሉትን እቀበለዋለሁ" ይላል።

አብሂላሽ የጋዜጠኛውን እስር በቅርብ እየተከታተለው ሲሆን ሁኔታውንም ፖለቲካዊ ጥቃት ይለዋል።

አክሎም "የጋዜጠኛው መሰረታዊ መብቶች ተጥሰዋል" በማለትም ይከራከራል።

በርካታ ተችዎች የኡታር ፕራዴሽን አስተዳደርም እያወገዙ ይገኛሉ። በተለይም የእስልምና እምነት ተከታዮችን ኢላማ በማድረግና አወዛጋቢ በሆነው የሂንዱ መነኩሴ ዮጊ አዲትያናት አመራር ጋር በተያያዘ ግዛቲቷ ከፍተኛ ትችቶችን እያስተናገደች ትገኛለች።

ዮጊ አዲትያናት በሕንድ ውስጥ በከፋፋይና ፀብ አጫሪ ፖለቲከኛነቱ የሚታወቅ ሲሆን በተለይም በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ፀረ-እስልምና ሁኔታዎችን በማነሳሳት ይወቀሳሉ።

የእሳቸው አስተዳደርም ሆነ የአካባቢው የፖሊስ ኃይል በደቦ ተደፍራ የተገደለችው ግለሰብ ጋር በተገናኘ ዓለም አቀፍ ውግዘትን አስተናግደዋል።

በተለይም ባለስልጣናቱ የቤተሰቧን ፍቃድ ሳያገኙና ሚዲያውን አርቀው በሌሊት ግለሰቧን መቅበራቸው በርካታ ጥያቄዎችን አጭሯል።

የግለሰቧን ተደፍሮ መገደል ለመቃመወም የወጡ ሰዎችን ፖሊሶች ሲደበድቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የግለሰቧን ተደፍሮ መገደል ለመቃመወም የወጡ ሰዎችን ፖሊሶች ሲደበድቡ

የግለሰቧን መሞት ተከትሎ በነበሩ ቀናት መላውን ሕንድ ያናወጡ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።

በኡታር ፕራዴሽ ግዛት የፀጥታ ኃይሎች የጥቃት ሰለባ የሆነችውን ግለሰብ ቤተሰቦች ለማፅናናት የሚሄዱ ሰልፈኞችን መደብደባቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ውግዘትን አስተናግደዋል።

በፖሊስ ከተጎሸሙት መካከልም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ይገኙበታል ተብሏል።

እኔና ጋዜጠኛ ሲዲሂኬ ወደ አካባቢው ከማምራታችን ከአንድ ቀን በፊት የግዛቲቷ አስተዳዳሪ ዮጊ አዲትያናት የግዛቲቷን ስም ለማጠልሸት ዓለም አቀፋዊ የሆነ ሴራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ይሄንንም ሁኔታ በግዛቲቷ ብልፅግና የተናደዱ ሰዎች እየተጠቀሙበት ነው ብለዋል።

የጋዜጠኛው እስር በርካታ የነፃነት ታጋዮችን ስጋት ውስጥ ጥሏቸዋል። ሕንድ ለጋዜጠኞች የምታሰጋ አገር ሆናለችም እያሉ ነው።

ባለፈው ዓመት የጋዜጠኞችን ሁኔታ በሚገመግመው የወርልድ ፕሬስ ፍሪደም ኢንዴክስ የሰንጠረዥ ደረጃ ከ180 አገራት መካከል 142 ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ይህንን ዓመታዊ ሪፖርት የሚያዘጋጀው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ካለፈው ዓመት ሁለት ደረጃ እንደወረደችም አስታውቋል።

በያዝነው ዓመት የካቲት ወር ላይ በዴልሂ የተደረገውን የአርሶ አደሮች አመፅ የዘገቡ ስምንት ጋዜጠኞች ላይ የወንጀል ክስ ተመስርቷል።

በተለይም ይህ ሁኔታ በሴት ጋዜጠኞችና በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የሚፀና ሲሆን በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ላይ ከፍተኛ ውርጅብኝን ያስተናግዳሉ።

አብሂላሽ እንደሚለው ፖሊስ በጋዜጠኛ ሲዲሂኬ ላይ ምንም አይነት መረጃ ማቅረብ አለመቻሉን ነው።

ነገር ግን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጠበቃ እንደሚለው የአካባቢው ባለስልጣናት የተሳካላቸው ነገር ቢኖር ወደ ሃትራስ ሄደው ዘገባ መስራት የሚፈልጉ ጋዜጠኞችን ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ሆኗል፤ ወደ ቦታው ከመሄድም ከልክሏቸዋል።

የሲዲሂኬ ጠበቃ በበኩላቸው "የጋዜጠኛ እስር ከሌላ ሰው እስር ጋር ይለያያል" ይላሉ "ምክንያቱም ሚዲያን ዝም ማሰኘት ማለት የዲሞክራሲ መጨረሻ ነው" ብለዋል።