"በህይወት መቆየት አልፈልግም ነበር" ሜጋን መርክል

ሜጋን መርክልና ሃሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰሴክስ ደችስ በመባል የምትታወቀው ተዋናይት ሜጋን መርክል በእንግሊዝ የንጉሳውያን ቤተሰብ የነበራት ህይወት ከመክፋቱ የተነሳ "በህይወት መቆየት አስጠልቷት" እንደነበር ይፋ አድርጋለች።

ረዘምና ጥልቀት በነበረው የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ሜጋን ለኦፕራ ዊንፍሬይ እርዳታ ብትፈልግም የሚሰጣት አካል እንዳልነበር ተናግራለች።

የሜጋንን የግል ህይወት በዝርዝር በዳሰሰው በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይ በተለይም ልጃቸው አርቺ" ምን ያህል ጥቁር ይሆናል?" የሚል ጥያቄ ከንጉሳውያን ቤተሰብ አባል ለሃሪ መጠየቁ በህይወቷ ያስከፋት ወቅት መሆኑንም አልደበቀችም።

ኦፕራ ከቃለ መጠይቁ በኋላ ይህንን አስተያየት የሰጡት የእንግሊዟ ንግስት ወይም የኤድንብራው ዱክ አለመሆናቸውን ሃሪ መናገሩን አስታውቃለች።

በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ከኦፕራ ጋር የተደረገው ቃለ መጠይቅ በአሜሪካ ቴሌቪዥን፣ ሲቢኤስ ስፔሻል ሲሆን የተላለፈው ጥንዶቹም አልተከፈላቸውም ተብሏል።

ሁለት ሰዓት ያህል እርዝማኔ ባለው በዚህ ቃለ መጠይቅ ዘረኝነት፣ የአእምሮ ጤና፣ ከሚዲያው ጋር ስለነበራቸው ግንኙነትና የንጉሳውያኑ ቤተሰብ ስለነሱ ያለውን እይታ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።

ጥንዶቹ ካነሷቸው አንዳንድ ሃሳቦችም መካከል

  • በዚሁ ቃለ መጠይቅ ሁለተኛ ልጃቸው ሴት እንደሆነች ተናግረዋል።
  • በይፋ በአውሮፓውያኑ 2018 ከመጋባታቸው ሶስት ቀናት ቀደም ብሎ በቤታቸው ጀርባ በኤጲስ ቆጶስ ካንተርበሪ በተመራ ዝግጅት ቃለ መኃላ ፈፅመዋል።
  • ሃሪ ወንድሙና አባቱ በንጉሳውያን ስርአት ውስጥ ወጥመድ ውስጥ ናቸው ብሏል።
  • አባቱ ከባለፈው አመት ጀምሮ ገንዘብ መስጠት ማቆሙንና ስልኩንም እንደማያነሳ ተናግሯል።

ባለትዳሮቹ ከንጉሳውያን ቤተሰብ ኃላፊነታቸው እንደተነሱ ይፋ አድርገው ወደ ካሊፎርኒያ መኖሪያቸውን ያደረጉት ባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ ነው። በባለፈው ወርም ጥንዶቹ ወደ ኃላፊነታቸው እንደማይመለሱ ተነግሯል።

ሜጋን እንዳለችው ማከናወን በምትችላቸው ጉዳዮች ላይ ገደብ በመጣሉ በከፍተኛ ሁኔታ የብቸኝነት ስሜት ይሰማት እንደነበር አጋርታለች፤ ለወራት ያህልም ከቤት አትወጣም ነበር።

በአንድ ወቅትም "ከዚህ በላይ መቼም ቢሆን ብቸኝነት እንደማይሰማኝ አወቅኩኝ" በማለት ለኦፕራ ተናግራለች።

ኦፕራም በበኩሏ ራሷን ለመጉዳት ወይም ራሷን ለማጥፋት አስባ እንደሆነ በጠየቀቻት ወቅት የ39 አመቷ ሜጋን " አዎ! በጣም ግልፅ ነበር። በጣም አስፈሪ ነበር። ለማን ማዋየት እንዳለብኝ አላውቅም ነበር" ብላለች።

ሜጋን እንደምትለው ከሃሪ ጋር በሮያል አልበርት አዳራሽ አንድ ዝግጅት ቆይተው ሲወጡ አንድ ፎቶግራፍ "ማደን" በሚባል ሁኔታ እያሳደዳት እንደነበር ተናግራ በወቅቱም "ነፍሰ ጡር ነበርኩ" ብላለች።

"ወደ ዝግጅቱ ልንሄድ ስንል ከሃሪ ጋር እያወራን ነበር" ያለችው ሜጋን

ኦፕራም "በህይወት መቆየት እንደማትፈልጊ? " ብላ ጠየቀቻች

ሜጋንም ምላሿ "አዎ" ነበር

የዚያን ምሽትም ዝግጅት የተገኘቸው በቤት ውስጥ ብቻዋን መቆየቷ አስጊ ስለነበር መሆኑን ገልፃ በዝግጅቱም ወቅት ሃሪ እጇን ጠበቅ አድርጎ ይዟት እንደነበር አስታውሳለች።