ሠራተኞቹ 'የዘረኝነት ጥቃት ሲደርስባቸው' እረፍት እንዲወጡ የሚያስገድደው' ጉግል

የጉግል አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጉግል አሜሪካ ውስጥ ሠራተኞቹ የዘረኝነትና ፆታዊ ጥቃት ሲደርስባቸው የሕክምና እረፍት እንዲወስዱና የአእምሮ ጤና ሐኪም እንዲያማክሩ እንደሚያደርግ ተነገረ።

ይህንን የዘገበው ኤንቢሲ የተሰኘው ጣቢያ ነው።

አንድ የጉግል ሠራተኛ ስለደረሰው ጥቃት የጉግል የሰው ኃይል የሕክምና እረፍት እንዲወስዱ ማስገደድን ልማድ እንዳደረገው ይናገራሉ።

በቅርቡ ሁለት የጉግል 'አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኤቲክስ' [ሰው ሰራሽ ልህቀት ሥነ-ምግባር] አጥኚዎች ስለዘር ስብጥር በማንሳታቸው በኩባንያው መባረራቸውን አሳውቀው ነበር።

ጉግል መሰል ድርጊቶችን አልፈፀምኩም ሲል አስተባብሎ፤ በተነሳው ክስ ላይ ምርመራ እንደሚያደርግ ተናግሯል።

"ሠራተኞች የሚያነሱት ቅሬታ የሚታይበት ሥርዓት አለን። በጣም ግልፅ በሆነ መንገድ ነው ለመሥራት እንጥራለን" በሏል ኩባንያው በለቀቀው መግለጫ።

"ፖሊሲዎቻችንን የሚጥሱ ሠራተኞች ላይ ከበድ ያለ እርምጃ እንወስዳለን" ብሏል ድርጅቱ።

የቀድሞ የጉግል ሠራተኛ የሆነው ቤንጃሚን ክሩዝ የቆዳ ቀለሙን በተመለከተ አንድ ሌላ ሠራተኛ የሰጠውን አስተያየት በተመለከተ ለሰው ኃይል ቅሬታ ማቅረቡን ለኤንቢሲ ተናግሯል።

"ቅሬታውን ካቀረብኩ በኋላ ሥራዎቼ ከእኔ ይነጠቁ ጀመር። ነገር ግን የቡድኔ አባላት ምን እንዳልተፈጠረ ነበር የሚሆኑት" ሲል ለጣቢያው ተናግሯል።

"የሕክምና እረፍት እንድወስድ ከመከሩኝ በኋላ ሁሉን ነገር በፍጥነት ነበር ያስኬዱት" ይላል።

ሌላ የቀድሞ የጉግል ሠራተኛ ደግሞ "ባለፈው ዓመት በደረሰባቸው ነገር ብቻ የአእምሮ ሕክምና እረፍረት እንዲወስዱ የተደረጉ በትንሹ 10 ሰዎች መጥቀስ እችላለሁ" ይላሉ።

የኤንቢሲ የምርመራ ዘገባ አንድ ደርዘን የጉግል ሠራተኞች ሆነው ይህ ጉዳይ የደረሰባቸው ሰዎችን ታሪክ ይፋ አድርጓል።

ከእነዚህ መካከል ባለፈው ዓመት [2020] ሥራቸውን ያጡት የሰው ሰራሽ ልህቀት ባለሙያዎቹ ትምኒት ገብሩና ማርጋሬት ሚቼል ይገኙበታል።

ከጉግል መባረሯ ዓለም አቀፍ ማዕበል የፈጠረውና ጉግልን ያስተቸው ትምኒት ገብሩ [ዶ/ር] ከመባረሯ በፊት የስነ-ልቡና አማካሪ እንድታይ ምክር እንደተሰጣት ትናገራለች።

ከሥራ ከመባረሯ በፊት በይፋ ትምኒትን የደገፈችው የሙያ አጋሯ ማርጋሬት ሚቼል [ዶ/ር] የኤንቢሲ የምርመራ ዘገባ የሷንም ሂደት የሚያንፀባርቅ እንደሆነ በትዊተር ገጿ ፅፋለች።

ማርጋሬት አክላ ዘገባው በጣም ከባድ ቢሆንም 'የተደበቀ እውነታን ማጋለጡ' አስፈላጊ ነው ብላለች።

ጉግል የተሰባጠረ የሰው ኃይል የለውም ተብሎ የሚተች ብቸኛው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አይደለም።

ባለፈው ሳምንት አንድ የአሜሪካ ኤጀንሲ ፌስቡክ ሰው ሲቀጥር ሕቡዕ በሆነ መንገድ ዘረኝነት አለበት ሲል ምርመራ እያደረገበት እንደሆነ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ቅሬታውን ያቀረቡት ለሥራ ማመልከቻ ዶኪዩመንታቸውን የላኩ አራት ሰዎች ናቸው።

የፌስቡክ አፈ ቀላጤ አንዲ ስቶን ስለጉዳዩ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።