ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ የተከተቡ ዜጎቿ ጭምብል ሳያደርጉ መሰባሰብ ይችላሉ አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ) የኮሮናቫይረስ ክትባት የተከተቡ ሰዎች ወደቀደመ ህይወታቸው መመለስ ይችላሉ የሚል መመሪያ አውጥቷል።
በዚህም መሰረት ክትባቱን የተከተቡ ሰዎች ጭምብል (ማስክ) ሳያደርጉ በቤት ውስጥ መሰብሰብ ይችላሉ ተብሏል።
ሲዲሲ እንዳስታወቀው የመጨረሻውን ክትባት ከተከተቡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ከኮሮናቫይረስ ስጋት ነፃ ናቸው ብሏል።
እስካሁን ድረስ አሜሪካ ከ30 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን ከትባለች።
የአገሪቱ የጤና ባለስልጣናት አዲሱን የደህንነት መመሪያ ይፋ ያደረጉት በትናንንትናው እለት ዋይት ሃውስ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ግብረ- ኃይል መግለጫ ላይ ነው።
መመሪያው የኮሮናቫይረስ ክትባትን የወሰዱ ሰዎች ማድረግ ይችላሉ ብሎ ካስቀመጣቸው መካከል፦
- ከተከተቡ ሰዎች ጋር ያለ ጭምብልም ሆነ አካላዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ በቤት ውስጥ መገናኘት
- በአንድ ቤት ውስጥ ከሚኖሩና ተደራራቢ ህመም የሌላቸው ወይም ተጋላጭ የማህበረሰቡ አካላት ካልሆኑ ካልተከተቡ የቤተሰብ አባላት ጋር በቤት ውስጥ መገናኘት
- በኮቪድ-19 ቢጋለጡም ምርመራዎችን አያደርጉም እንዲሁም ለይቶ ማቆያ ውስጥ አይገቡም፤ ምልክት እስካላሳዩ በስተቀር።
"ከኮቪድ-19 በኋላ ሊኖር የሚችለውን አለም ማየት ጀምረናል። የበለጠ ዜጎቻችን በተከተቡ ቁጥር ማከናወን የምንችላቸውን ተግባራትም ይጨምራሉ" በማለት የዋይት ሃውስ ከፍተኛ አማካሪ አንዲ ስላቪት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን ክትባቱን የተከተቡ ሰዎች ህዝባዊ በሆነ ቦታ ላይ ጭምብል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፤ እንዲሁም አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማስወገድና የተጣሉ የጉዞ ገደቦችን መከተል ይኖርባቸዋል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ መመሪያው ያልተከተቡና ለኮሮናቫይረስ በበለጠ ተጋላጭ ከሆኑ ማህበረሰቦችም በተለይ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አስቀምጧል።
አሜሪካ በቅርቡ የምትከትባቸውን ዜጎቿን ቁጥር በከፍተኛ እየጨመረ መሆኑን ያስታወቀች ሲሆን እስካሁን ድረስ 90 ሚሊዮን ሰዎች ተከትበዋል። በተለይም የጆንሰን ጆንሰን የአንድ ጊዜ ክትባት እውቅና ማግኘቱ አቅርቦቱን ጨምሮታል ተብሏል።
ነገር ግን በኮሮናቫይረስ ክፉኛ በተመታችው አሜሪካ ኮቪድ-19 የማህበረሰቡ የጤና ጠንቅ መሆኑ ቀጥሏል።
አገሪቱ እስካሁን ድረስ 29 ሚሊዮን ዜጎቿ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ያስታወቀች ሲሆን 525 ሺህ ዜጎቿንም አጥታለች።












