ህዳሴ ግድብ፡ ሱዳንና ግብጽ በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች እንዲሳተፉ ጠየቁ

የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ እና የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄነራል አል ቡርሐን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ እና የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄነራል አል ቡርሐን

ግብጽና ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርጉት ድርድር ላይ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች እንዲሳተፉ በድጋሚ ጥሪ አቀረቡ።

በተለይ በሱዳን በኩል ሲቀርብ የነበረው ይህን ጥያቄ፣ ቅዳሜ ዕለት ካርቱምን የጎበኙት የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ከሱዳን ሲቪልና ወታደራዊ መሪዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ በድርድሩ ተጨማሪ አሸማጋዮች እንዲሳተፉ በጋራ ጠይቀዋል።

ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ግዙፍ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ዙሪያ አዲስ ዙር ድርድር ላይ ከአፍሪካ ሕብረት፣ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ሕብረትና ከተባበሩት መንግሥታት የተውጣጡ አሸማጋዮች የሚሳተፉበት እንዲሆን ጠይቀዋል።

ከዚህ ቀደም ለወራት በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በሦስቱ አገራት መካከል ሲካሄድ የቆየው እና መቋጫ ባላገኘው ድርድር ላይ ሌሎች አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሳተፉ የቀረበውን ጥያቄ ኢትዮጵያ አለመቀበሏ ይታወሳል።

ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት እየተከናወነ ባለበት ወቅት ሌሎች አደራዳሪዎች ይግቡ ማለት "የድርጅቱን አስተዋፅኦ የሚያኮስስ ነው" ብለዋል።

የቀድሞው አምባገነን መሪ ኦማር አልበሽር በሕዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሱዳንን ለመጀመሪያ ጊዜ እየጎበኙ ያሉት የግብጹ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ "በአስቸኳይ ፍትሃዊ፣ ሚዛናዊና አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት" ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ከግዛቷ 85 በመቶ ያህል ውሃ ከምታበረክተበት ከአባይ ወንዝ ውሃ ለመጠቀም ያላትን መብት ለድርድር የማታቀርብ መሆኑን መግለጿ ይታወሳል።

ይህ ወደ መጠናቀቁ የተቃረበው ግዙፍ ግድብ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌቱ ተካሄዷል።

ሱዳንና ግብጽ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ለማካሄድ ያቀደችው ሁለተኛው ዙር የግድቡን ውሃ ሙሌት ከመጀመሯ በፊት ስምምነት መደረስ አለበት እያሉ ነው።

ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው የህዳሴ ግድብ ከአባይ ወንዝ በሚያገኙት የውሃ መጠን ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል በሚል ስጋታቸውን ከመግለጻቸው ባሻገር ለዓመታት ሲካሄድ የቆየው ድርድር መቋጫ እንዳያገኝ አድርጎታል።

በሦስቱ አገራት መካከል ያለውን አለመግባባት በውይይት ለመፍታት ለዓመታት የዘለቀ ውይይት ቢካሄድም፣ ሁሉንም በሚያስማማ ሁኔታ ሳይቋጭ አስካሁን የቆየ ሲሆን በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት ሲካሄድ በቆየው ድርድር ግብጽና ሱዳን በአንድ ላይ በመቆም ጥቅማቸውን ለማስከበር እየጣሩ ነው።

የግብጹ ፕሬዝዳንት የሱዳን ጉብኝት ባለፉት ሳምንታት የሁለቱ አገራት ሲቪልና ወታደራዊ ከፍተኛ ባለስልጣናት በካርቱምና በካይሮ ጉብኝትና ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

ከዚህ ውስጥም ባለፈው ማክሰኞ የሁለቱ አገራት በከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት በተከታታይ ሲያካሂዱ የነበረውን ውይይት አጠናቅቀው የጋራ ወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ቀደም ሲልም ሱዳንና ግብጽ ከዚህ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ያደረጉ ሲሆን ተመሳሳይ ልምምዶች በቀጣይነት እንደሚኖሩ ተነግሯል።

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የድንበር ውዝግብ ውስጥ ከገባች ወራት ተቆጥረዋል።

ይህም ባለፈው ጥቅምት መጨረሻ ሱዳን ወታደሮቿን በማሰማራት በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል፣ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ሰፍረውበት የነበሩትንና የግዛቴ አካል ናቸው የምታላቸው ቦታዎች በቁጥጥሯ ስር ማስገባቷ ይታወሳል።

ኢትዮጵያም በሱዳን ሠራዊት ወረራ እንደተፈጸመባት በመግለጽ ወታደሮቿ ከግዛቷ እንዲወጡና የድንበሩ ጉዳይ ቀደም ሲል በተጀመረው ውይይት እንዲፈታ እየጠየቀች ትገኛለች።