በህዳሴ ግድብ ላይ ሌሎች አደራዳሪዎች ይግቡበት ማለት የአፍሪካ ህብረትን አስተዋፅኦ የሚያኮስስ ነው-ኢትዮጵያ

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት እየተከናወነ ባለበት ወቅት ሌሎች አደራዳሪዎች ይግቡ ማለት የድርጅቱን አስተዋፅኦ የሚያኮስስ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው ዕለት የካቲት 24፣ 2013 ዓ. ም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም ነው ይህንን የተናገሩት።
ከሰሞኑ ሱዳን ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ በአሸማጋይነት እንዲገቡበትና ኢትዮጵያ በብቸኝነት የምታደርገው የውሃ ሙሌት ግድቡን ይጎዳል ማለቷ ተዘግቧል።
ቃለ አቀባዩ በዛሬው መግለጫቸው በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ለሁሉም አካላት እንደሚጠቅም አስታውሰው ድርድሩም አልተቋጨም ብለዋል።
ድርድሩ ባልተቋጨበት ወቅት ሌሎች አደራዳሪዎችን መጋበዙ የድርጅቱን አስተዋፅኦ እንደሚያኮስሰውም ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የሶስትዮሽ ድርድር አራዝማዋለች መባሉ ተጨባጭነት የሌለው ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሶስትዮሹን ድርድር የምታካሂደው ውሃዋን የመጠቀም መብቷን መሰረት ባደረገና ሁለቱን የታችኛው ተፋሰስ አገራትን በማይጎዳ መልኩ በመርሆች ስምምነት መመሪያዎችን በተከተለ መሆኑንን ዲና ሙፍቲ አስታውሰዋል።
እስካሁንም ባለው የድርድር ሂደት የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነትን ቦታ በቅርቡ የተሰናበተችውን ደቡብ አፍሪካን አመስግነው ቦታውን ለተረከበችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይኸው ሂደት እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለዓመታት ሲካሄድ የነበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ፍሬ ሳያፈራ ሶስቱንም አገራት አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል።
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ግብጽ የቅኝ ግዛት ውሎችን ሙጥኝ እንዳለችና ኢ-ፍትሃዊና አግላይ የሆነውን ስምምነት ተቀባይነት እንዲያገኝ ጫና እያደረገች ነው በማለትም ትወቀሳለች።
ባልነበረችበት የተፈረመ ስምምነት ለናይል ወንዝ 77 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ለምታመነጨው ኢትዮጵያ ምንም ድርሻ የማይሰጥና ተፈጥሯዊም ሆነ ሕጋዊ መብቴን የሚነጥቅ ነው በማለትም ኢትዮጵያ ትከራከራለች።
ግብጽ ከምታነሳቸው ቅሬታዎች መካከል ኢትዮጵያ ግድቡን ሙሉ አቅም እየተጠቀመች ድርቅ ቢያጋጥም ችግሩ የሦስቱም አገራት ጉዳይ ነው የሚል አቋም ላይ መድረሷን ነው።
ረዘም ላለ ጊዜ ድርቅ የሚከሰት ከሆነ ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጥቅምን ለመጠበቅ ዋስትና ልትሰጠን ይገባል በማለትም ግብጽ ትከራከራለች።
ኢትዮጵያ ያለ ታችኛው ተፋሰስ አገራት ስምምነትም ግድቡን ለመሙላት መወሰኗም ሁለቱን አገራት የማስገደድ ውሳኔ ነው ይላሉ ግብፅና ሱዳን።
"በትግራይ እየተደረገ ስላለው እርዳታ"
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው ዕለትም በግጭት በተጎዳችው የትግራይ ክልል መንግሥታቸው እያደረገ ስላለው ሁኔታም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ ለሚፈልጉ ከመቶ በላይ አለም አቀፍ ድርጅቶች ፍቃድ መስጠቷን አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ እንዲንቀሳቀሱ ፍቃድ የተሰጣቸው አለም አቀፍ ድርጅቶች ቁጥር 135 መሆኑን ገልፀው ከነዚህ ውስጥ ቢቢሲና አልጀዚራን ጨምሮ 11ዱ ሚዲያዎች ናቸው ብለዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ መንግሥታቸው በክልሉ ባለው ሁኔታ የሚቀርብበት ትችት ትክክለኛ እንዳልሆነ ገልፀው "በትግራይ ክልል ያልተቋረጠ ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ ነው" እንዲሁም 70 በመቶ የሚሆነው እርዳታ እየተሸፈነ ያለውም በኢትዮጵያ መሆኑን አመላክተዋል።
የተለያዩ አለም አቀፍ አካላት እርዳታ አናሳ ነው ያሉት ቃለ አቀባዩ "ትችት ያለ ድጋፍ የተጎዳውን ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥትን አይጠቅምም" ብለዋል።
የአለም አቀፉ የምግብ ድርጅት ኃላፊ ዴቪድ ቢስሊይን ዋቢ አድርገው በክልሉ ለሚደረገው ድጋፍ 107 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደሚያስፈልግና መንግሥታቸውም አለም አቀፉን ድጋፍ እንደሚሻ ጠቁመዋል።
በክልሉ እስካሁን ድረስ 3.5 ሚሊዮን ነዋሪዎችም እርዳታ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
ከትግራይ ክልል ግጭት ጋር በተያየዘ የተነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ግድያዎችን በተመለከተም ቃለ አቀባዩ መንግሥት ከፌደራል ፖሊስ፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ጋር በመጣመር ተፈፀሙ የሚባሉ ወንጀሎችን ይመረምራል ብለዋል።
የነዚህን አካላት ምርመራ መሰረት በማድረግም መንግሥት ጥፋት ያጠፉትን አካላት ወደ ፍትህ እንደሚያቀርብ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በምርመራው ላይ ተጨማሪ እርዳታ ካስፈለገ መንግሥት የውጭ አካል ሊጋብዝ እንደሚችል ጠቆም አድርገዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአክሱም ተገድለዋል የሚለውን የአምነስቲን ሪፖርት አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርትም በአክሱም ዝርፊያዎች፣ መደፈሮች እንዲሁም የንፁኃን ዜጎች መሰረተ ልማት መውደሙን አረጋግጧል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሚያደርጉት ምርመራ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአለም ህዝብ በወቅቱ እንደሚያሳውቁ ጨምረው ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል የኤርትራ ወታደሮች በኅዳር ወር በሁለት ቀናት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደላቸውን በተመለከተ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የወጣው ሪፖርት "ባልተሟላ መረጃና ውስን በሆነ የጥናት ዘዴ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው" ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት መተቸቱ ይታወሳል።
አምነስቲ በበኩሉ በነዚህ ቀናት የተፈፀመው የቡድን ግድያ በሰብኣዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ሊሆን ይችላል በማለት በሪፖርቱ አስቀምጧል።
ጥቅምት 4፣ 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት በመፈፀሙ መንግሥት "ህግ የማስከበር" ወታደራዊ ዘመቻን ማካሄዱን ገልጿል።
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን ቢገልጽም በአንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወታደራዊ ግጭቶች እንዳሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።












