ሜጋንና ሃሪ ከኦፕራ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለእንግሊዝ ንጉሣውያን ምን አሉ?

የፎቶው ባለመብት, Harpo Productions - Joe Pugliese
በበርካቶች ሲጠበቅ የነበረው የሰሴክሱ ልዑል ሃሪና ባለቤቱ ሜጋን ከኦፕራ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ በርካታ አነጋጋሪ ጉዳዮችን ይዞ ቀርቧል።
ንጉሣዊ ኃላፊነት በቃን ብለው ከባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ወጥተው አሁን መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉት ጥንዶቹ በቃለ-ምልልሱ ስለግላዊ ሕይወታቸውና ስለ እንግሊዝ ንጉሣዊያን ቤተሰቦች ዘክዝከዋል።
ባልና ሚስት ከንጉሣዊያን ጋር ስላላቸው ግንኙነት፣ ስለዘረኝነት እንዲሁም ስለአእምሮ ጤንነታቸው አውግተዋል።
ሜጋን ከኦፕራ ጋር ረዘም ያለ ቆይታ ካደረገች በኋላ ባለቤቷ ሃሪ ዘግየት ብሎ ነበር የተቀላቀላቸው።
ከቃለ-ምልልሱ መካከል አነጋጋሪ የሆኑ ጥቂት ነጥብ እናንሳ።
1• የሜጋን ልጅ ጥቁር ይሆን ወይ?
ጥንዶቹ በቃለ-ምልልሱ ላይ ካነሷቸው ክሶች መካከል አንዱ ንጉሣዊያን ቤተሰቦች ዘንድ የተነሳው የሜጋንና የሃሪ ልጅ የቆዳ ቀለም ጉዳይ ይጠቀሳል።
"ነፍሰጡር በነበርኩ ወቅት ልጁ ሲወልድ ቆዳው ምን ያህል ይጠቁር ይሆን የሚለውን የተመለከተ በርካታ ውይይት ነበር" ብላለች ሜጋን።
ሜጋን እነዚህ ውይይቶች የተካሄዱት ከሃሪ ጋር ነበር ትላለች። ጥንዶቹ የትኛው የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል ይህን እንዳለ ከመናገር ተቆጥበዋል።
"ስለዚህ ጉዳይ ያወራነውን ማጋራት አልሻም፤ በወቅቱ ጉዳዩን መነሳቱ አስደንግጦኝ ነበር" ብሏል ሃሪ።
ሃሪ፤ አክሎ ቤተሰቦቹ ጋዜጦች ላይ የሚወጡ "የቅኝ ገዢ" አተያይ ያላቸውን ፅሑፎች በተመለከተ ምንም አለማለታቸው እንደጎዳው ተናግሯል።
2• ኬት 'ሜጋንን አስለቀሰቻት እንጂ ተቃራኒው አልሆነም'
ከጥቂት ዓመታት በፊት በጋዜጦች ላይ የወጣ አንድ ታሪክ ነበር። የኬምብሪጅ ልዑል ሚስት የሆነችው 'ኬት ከሜጋን ጋር ተጋጭታ አለቀሰች' ይላል ይህ ታሪክ።
ነገር ግን ሜጋን ለኦፕራ የሆነው ተቃራኒው ነው ስትል ነግራታለች።
"ሠርጋችን ሊደርስ ትንሽ ቀናት ሲቀሩት ኬት አበባ በምትይዘው ልጅ ልብስ ደስተኛ አልነበረችምና ይህ ጉዳይ ነው እንዳነባ ያደረገኝ" ብላለች ሜጋን።
ሜጋን በቃለ-ምልልሷ ኬት ዘግየት ብላ ይቅርታ እንደጠየቀቻትም ገልጻለች።

የፎቶው ባለመብት, PA
3• ሜጋን ራሷን ለማጥፋት ብትቃረብ እንኳ የሚረዳት አላገኘችም
ሜጋን ንጉሣዊውን ቤተሰብ ከተቀላቀለች በኋላ ምን ያህል ብቸኛ እንደነበረችና ነፃነቷን እንደተነፈገች ተናግራለች።
"ንጉሣዊውን ቤተሰብ ከተቀላቀልኩ ወዲህ ፓስፖርቴን፣ መንጃ ፈቃዴን፣ ቁልፎቼን ሁሉ አሳልፌ ሰጠሁ። ከዚያ በኋላ እነዚህን ንብረቶች ያገኘሁት ወደዚህ [አሜሪካ] ስመጣ ነው።"
እሷ እንደምትለው የአእምሮ ጤናዋ በጣም ከመቃወሱ የተነሳ "መኖር ሁሉ አስጠልቷት" ነበር።
"የሆነ ቦታ መሄድ እፈልጋለሁ፤ እርዳታ ማገኘት እፈልጋለሁ። እንደዚህ ዓይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም፤ ፍቀዱልኝ ልሂድ ስል መሄድ አትችይም ተባልኩኝ።"
ሜጋን እንደምትለው በንጉሣዊው ቤተሰብ 'ታላቅ ወደሚባሉት' እንዲሁም ወደ ቤተ-መንግሥቱ ቁልፍ ሰው ብትሄድም እርዳታ ልታገኝ አልቻለችም።
"ምንም ነገር ሊያደርጉልኝ አልፈቀዱም" ትላለች።
4• ሜጋን ከዳያና ጓደኞች ጋር አውርታለች
በአብዛኛው ከሜጋን ጋር የተመሳሰለ ታሪክ እንዳላት ሆና የሃሪ እናት የሆነችው ልዕልት ዳያና በቃለ-ምልልሱ ስሟ ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል።
በችግሬ ወቅት "ወደየት መሄድ እንዳለብኝ አላውቅም ነበር" የምትለው ሜጋን "ካገኘኋቸው ሰዎች መካከልና አሁንም ከማናግራቸው ሰዎች መካከል አንዷ የባለቤቴ እናት ጓደኛ ናቸው" ትላለች።
"ምክንያቱም ቤተ-መንግሥቱ ውስጥ በሚከናወነው ጉዳይ ማን ሊረዳ ይችላል?"
5• ሃሪ በቻርልስ እንደተካደ ተሰምቶታል
ቃለ-ምልልስ አድራጊዋ ኦፕራ፤ ሃሪ ከቤተሰቦቹ ጋር ያለው ግንኙነት በተለይ ደግሞ የዌልስ ልዑል ከሆኑት አባቱ ቻርልስ ከወንድሙ ጋር ያለው ግንኙነት ምን እንደሚመስል ጠይቃዋለች።
ሃሪ እንደሚለው ከንጉሣዊው ቤተሰብ ጋር ያላቸውን ውል ካቋረጡ በኋላ የሆነ ወቅት አባቱ "ስልክ አያነሳለትም" ነበር።
"እኔ በዚህ ጉዳይ እንደተካድኩ ነው የሚሰማኝ። ምክንያቱም እሱ ይሄንን ነገር ያውቀዋል። ደግሞ አርቺ [የሜጋንና ሃሪ ልጅ] የልጅ ልጁ ነው።"
"ነገር ግን ምን ቢሆን እኔ እወደዋለሁ። ቢሆንም በተፈጠረው ነገር እጅግ ተጎድቻለሁ። ግንኙነታችንን ማደስ ሁሌም ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ ነው።"
ስለ ወንድሙ ዊሊያምስ የተጠየቀው ሃሪ እንደሚወደውና ብዙ ነገር እንዳሳለፉ ተናግሮ "ነገር ግን አሁን ሁለታችን የተለያየ መንገድ ላይ ነን" ብሏል።
ነገር ግን ጥንዶቹ ከንግሥቲቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት መልካም መሆኑን ይናገራሉ።
ሃሪ ከአያቱ ጋር ያለው ግንኙነት መልካም እንደሆነ ተናግሯል። እንደውም ባለፈው ዓመት ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠ ስልክ እንደሚደዋወሉ ይናገራል።
6• ሃሪ 'ገንዘብ ተከልክሏል'
በፈረንጆቹ 2020 ሃሪ ከቤተ-መንግሥት የሚሰጠው 'የገንዘብ ድጎማ' ሙሉ በሙሉ እንደተቋረጠበት ተናግሯል።
ሃሪ፤ ኔትፍሊክስና ስፖቲፋይ የተሰኙ ገፆች ላይ መሥራት የጀመረው ለቤተሰቦቹ ገንዘብ ማምጣት ስላለበት አንደሆነ ይናገራል።
ጥንዶቹ እንደሚሉት ከዩናይትድ ኪንግደም ቤተ-መንግሥት የሚሰጣቸው ገንዘብ ሲቋረጥ አሜሪዊው ቢሊየነርና ጉምቱ የሚድያ ሰው ታይለር ፔሪ ነበር ከካናዳ ወደ ካሊፎርኒያ ሲዛወሩ ቤትና ጥበቃ ያቀረበላቸው።
ጥንዶቹ በቃለ-ምልልሳቸው በርካታ ጉዳዮችን አንስተዋል። ሜጋን ንጉሣዊውን ቤተሰብ ስትቀላቀል ብዙም ጥናት እንዳላደረገችና በብዙ ነገሮች እንደተደነቀች ተናግራለች።
ሜጋን ለመጀመሪያ ጊዜ ንግሥቲቱን ስታገኝ በርከክ ማለት እንደነበረባት አለማወቋን ትናገራለች።
ሜጋን አሁን ነፍሰጡር ናት። ጥንዶቹ ከወራት በኋላ ሴት ልጅ እንደሚኖራቸው አሳውቀዋል።

















