የእንግሊዙ ልዑል ሃሪ የአገሩ ሚዲያዎች የአዕምሮ ጤናው ላይ እክል እንደፈጠሩ ተናገረ

ሜጋንና ልዑል ሃሪ

የፎቶው ባለመብት, PA

የእንግሊዙ ልዑል ሃሪ የአገሪቱ ሚዲያዎች የባለትዳሮቹን ህይወት መበጥበጣቸውን ተከትሎ ቤተሰቦቹን ለመጠበቅ ሲል ከንጉሳዊው ኃላፊነት ራሱን ገሸሽ ማድረጉን አስታውቋል።

ፕሪንስ ሃሪ ቲቪ ቻት የተባለውን ፕሮግራም አዘጋጅ ጄምስ ኮርደን ጋር ባደረገው ቆይታ "ሚዲያው ስለኛ የሚዘግበው ጉዳይ የአእምሮ ጤናዬ ላይ እክል እየፈጠረ ነው"፤ "አባት ወይም ባለቤት እንደሚያደርገው ቤተሰቤን ቅድሚያ ሰጥቻለሁ" ብሏል።

የበኪንግሃም ቤተ መንግሥት ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው ልዑሉና ባለቤቱ ሜጋን መርክል ወደቀደመ የንጉሳውያን ቤተሰብ ኃላፊነታቸው እንደማይመለሱ አረጋግጧል።

ልዑሉ በበኩሉ ሙሉ በሙሉ መሰናበት ሳይሆን ጊዜያዊ ነው ብሏል።

ሁለተኛ ልጃቸውን እየጠበቁ ያሉት ባለትዳሮቹ፤ አርቺ ከተባለ የአንድ አመት ልጃቸው ጋር መኖሪያቸውን በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ አድርገዋል።

ከንጉሳዊው ስርዓት ኃላፊነትም ሙሉ በሙሉ መገለላቸውን ያሳወቁት በጥር ወር ላይ ነበር።

በወቅቱም የቤተ መንግሥት መጠሪያቸውንም ሆነ ገንዘብ እንደማይጠቀሙ አሳውቀው ነበር።

" በርካቶች የሆነውን እንዳዩት የሚረብሽ ወቅት ነበር። ሁላችንም የእንግሊዝ ሚዲያ እንዴት እንደሆኑ እውነታውን እንረዳለን። የአዕምሮ ጤናዬ ላይ ከፍተኛ እክል እያስከተለም ነበር፤ ይሄ መርዛማ ሁኔታም መቆም አለበት አልኩኝ" ብሏል ከጋዜጠኛው ጋር ባደረገው ቆይታ

ሆኖም እሱም ሆነ ባለቤቱ ህዝቡን ከማገልገል ስራቸው እንደማያፈገፍጉ ልዑሉ አስረድቷል።

ባለትዳሮቹ ከዚህ ቀደም አንድ ሚዲያን መክሰሳቸው ይታወሳል። ዘ ሜይል ሰንደይ የተባለውን ጋዜጣ ሜጋን ለአባቷ የፃፈችውን ደብዳቤ ማተሙን ተከትሎ ከሰውት የነበረ ሲሆን ብይኑም ለነሱ ሆኗል።

በወቅቱም ክሱን ያስገባችው ባለቤቱ ሜጋን ስትሆን ሁኔታው "ልቡን እንደሰበረውና" በአጠቃላይ ሚዲያዎች የከፈቱባትን ዘመቻ "ጭካኔ የተሞላበት" ብሎታል።

በህይወት የሌለችውን እናቱን ልዕልት ዲያናን በመጥቀስም "ከፍተኛ ፍራቻዬ ታሪክ ራሱን እየደገመ መሆኑ ነው" በማለትም በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

በቅርቡም ልዑል ሃሪ ይኸው ጋዜጣ ልዑሉ ለንጉሳውያን ስርዓቱ ጀርባውን ሰጥቷል በሚልም አንድ ፅሁፍ ማውጣቱን ተከትሎ ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨትም በሚል ከሷል።