የሕንድ አርሶ አደሮችን አመፅ ያጎላው የዕድሜ ባለፀጋው ፎቶ

ልዩ ፖሊስ አርሶ አደሩን በቆመጥ ሊደበድብ ሲል

የፎቶው ባለመብት, PTI

በሕንድ ከሰሞኑ አንድ ልዩ ፖሊስ በያዘው ቆመጥ በዕድሜ የጠኑ አንድ አርሶ አደርን ሲደበድብ የሚያሳይ ምስል ህንዳውያንን አስደንግጧል።

አርሶ አደሩ ሲክ ተብሎ የሚጠራው እምነት ተከታይ ሲሆን ጭንቅላታቸውም ላይ ጥምጣማቸውን ሸብ አድርገዋል።

ፎቶው የተነሳው ለፕሬስ ትረስት ኦፍ ኢንዲያ በሚሰራው የፎቶ ጋዜጠኛ ራቪ ቾድሃሪ ሲሆን በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ላይ በርካቶች ተጋርተውታል።

ከዚህም በተጨማሪ ፎቶው ለፖለቲካዊ አተካሮዎች ምክንያት ሆኗል።

በአገሪቱ ያሉት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ምስሉን እንደ አባሪ በመጠቀም መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ ጥቃት ያደርሳልም በማለት ለመተቸት ተጠቅመውበታል።

በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ባሃራቲያ ጃናታ ፓርቲ በኩሉ አርሶ አደሩ አልተደበደቡም፤ ወቀሳው ሐሰት ነው ይላል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች የሕንድን መዲና ዴልሂ መግቢያና መውጫዋን ተቆጣጥረውታል።

ባለፉት ቀናትም የአርሶ አደሮቹ አመፅ ሕንድን በተቃውሞ አንቀጥቅጧታል።

አርሶ አደሮቹ አገሪቷ በቅርቡ የተሻሻለው ሕግ ከጥቅማችን የሚቃረን ነው ይሉታል።

በሕንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮና በድህነት ከሚኖሩ መካከል አርሶ አደሮች ዋነኞቹ ናቸው። ከዚህ ቀደም የመንግሥት ፖሊሲዎች በነፃ ገበያ እንዳይጎዱም ሲጠብቃቸው ነበር።

ያ ግን አሁን ተቀይሯል። አዲሱ ሕግ ኮርፖሬሽኖችንና ከፍተኛ ገንዘብ ያላቸውን የሚጠቅምና ደሃ አርሶ አደሮችን አዘቅት ውስጥ የሚከት ነው ይላሉ።

ከዚህ ቀደም መንግሥት የግብርና ዘርፉን ገበያውን ይቆጣጠረው የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ግን እሱ ቀርቶ አርሶ አደሮቹ በቀጥታ ከግል ሻጮች ጋር ዋጋ መደራደር ይችላሉ።

አዲሱ ሕግ ከዚህ ቀደም ነጋዴዎች እህል ማከማቸት በወንጀል ይቀጣ የነበረውን በማሻሻል ማከማቸት ይችላሉ ይላል።

በዚህም በወረርሽኝ ወቅት ነጋዴዎች ዋጋ እንዲጨምሩ የሚያስችል ዕድል ሰጥቷል።

በሕንድ ከ86 በመቶ በላይ የሚሆኑት አርሶ አደሮች አነስተኛ መሬት ወይም ከሁለት ሄክታር በታች ያላቸው ናቸው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት ሁኔታ ጠቀም ባለና ለኑሯቸው በሚሆን ዋጋ ምርታቸውን ለትልልቅ ኩባንያዎች ለመሸጥ የመደራደሪያ አቅሙ የለንም ይላሉ።

የግሉ ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ የዘርና የማዳበሪያን ዋጋ በመጨመር ኑሯቸውን ከባድ አድርጎታል።

ከዚህ ቀደም መንግሥት ዝቅተኛ የዋጋ ድጋፍ የሚል ፖሊሲ የነበረው ሲሆን መንግሥት ሩዝና ስንዴ ለሚያመርቱ አምራቾች የሚሰጠው የዋጋ ነበረው።

በአዲሱም ሕግ ይህንንም ድጋፍ ያጣሉ ተብሏል።

መንግሥት በበኩሉ የግል ተቋማትን በግብርና ዘርፉ እንዲሳተፉ የፈቀደው ይህ ማሻሻያ አርሶ አደሮችን አይጎዳም በማለት ይከራከራል።

ይህ ግን ከአርሶ አደሮቹ ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም። አርሶ አደሮቹን ሳያሳትፍ የወጣ ሕግ ነው በሚል አመፁን አቀጣጥሎታል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችም ወደ መዲናዋ ዴልሂ ያቀኑ ሲሆን በከተማዋ መግቢያ በኩልም እንዳይገቡ ለማድረግ መሰናክልም ተደርጎባቸዋል።

አርሶ አደሮቹ በትራክተሮቻቸው ተጭነው እንዲሁም በእግራቸው ወደ መዲናወም ሲያቀኑ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶችና ልዩ የሠራዊቱ አባላትም ለማስቆም ሞክረዋል።

በዚህም ከፖሊስ ጋር ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሯል። በበርካታ አካባቢዎችም ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ በመርጨትና በውሃ በመበተን ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ለማድረግም ሞክሯል።

የአርሶ አደሮች ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ነጭ ፂማቸውን ያንዠረገጉት የሲክ እምነት ተከታዩ አርሶ አደርና የፖሊስ ቆመጥ ይዞ ሊመታቸው ሲሰነዝር የሚታየው የልዩ ፖሊስ አባል ፎቶ የተነሳውም በባለፈው ሳምንት አርብ ነው።

ተቃዋሚ አርሶ አደሮቹ በሰሜናዊ ምዕራብ ደልሂ በኩል በሲንኩ ድንበር በኩልም የተቀመጠውን መሰናክልም በማለፍ ወደ ከተማዋ ገብተዋል።

"ከፍተኛ የሆነ የድንጋይ መወራወር ነበር፤ ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ የተቀመጡ መሰናክሎች ተሰብረዋል። አውቶብስ ከጥቅም ውጭ ሆኗል። በፖሊስና በተቃዋሚ አርሶ አደሮችም መካከል ከፍተኛ ግጭት ነበር" በማለት የአርሶ አደሩን ፎቶ ያነሳው የፎቶ ጋዜጠኛው ራቪ ቾድሃሪ ቡም ላይቭ ለተባለ ድረ ገፅ ተናግሯል።

ፎቶ አንሺው ፖሊሶች አርሶ አደር ተቃዋሚዎችን መደብደብ መጀመራቸውንና በፎቶው ላይ ያሉት የዕድሜ ባለፀጋ አርሶ አደርም ተደብድበዋል ይላል።

ፎቶው በትዊተር፣ ፌስቡክና ኢንስታግራም ማኅበራዊ ድረገፆች አማካኝነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አጋርተውታል።

በርካቶችም በፎቶው ስር እንደ የጽሁፍ መግለጫ ያስቀመጡት "ጃይ ጃዋን፣ ጃ ኪሳን" የሚል ሲሆን ትርጉሙም "ክብር ለወታደሩ፤ ክብር ለአርሶ አደሩ" የሚል ነው።

ይህ መፈክር በጎሮጎሳውያኑ 1965 በሕንድና በፓኪስታን በተደረገው ጦርነት ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ላል ባሃዱር ሻስትሪ የተጠቀሙበት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በወቅቱ በአገር ግንባታ ላይ ወታደሮችና አርሶ አደሮች ያላቸውን አስተዋፅኦም አፅንኦት ለመስጠት ነው።

በምክር ቤቱ የተቃዋሚዎች ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ራውል ጋንዲም ፎቶውን በትዊተር ገፃቸው ለጥፈዋል።

"በጣም አሳዛኝ ፎቶ ነው። መፈክራችን ክብር ለወታደሩ፣ ክብር ለአርሶ አደሩ ነበር። ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ እብሪተኝነት አርሶ አደሩ ከወታደሩ ጋር እንዲፋጠጥና እንዲጋጭ አድርጎታል። ይህ አደገኛ ነው" በማለትም የምክር ቤት አባሉ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

Presentational white space
የ X ይዘትን ይለፉት, 1
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ, 1

Presentational white space

የገዢው ፓርቲ ቢጄፒ አመራር የሆኑት አሚት ማልቪያ በበኩላቸው ተቃዋሚውን ራውል ጋንዲን ለማሳጣት በሚል አርሶ አደሩ አልተመቱም፤ ፕሮፖጋንዳም ነው ብለውም የሶስት ሰኮንዶች ቪዲዮ በትዊተር ገፃቸው አጋርተው ነበር።

Presentational white space
የ X ይዘትን ይለፉት, 2
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ, 2

Presentational white space

ሆኖም በመጨረሻ የእሳቸው ትዊት ፕሮፖጋንዳ እንደሆነ ታወቀ። ትዊተር በኩሉ ቪዲዮው ተጨማሪ ነገሮች ገብተውት ለማስመሰል የተሰራ ነው ብሏል።

እውነተኛ መረጃዎችን በማደን የሚታወቀው ቡምላይቭ የተሰኘው ድረገፅ የክስተቱን ረዘም ያለ ቪዲዮና በፎቶው ላይ ያሉትን አርሶ አደር ሱክዴቭ ሲንግን ፈልጎም በማግኘት ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸዋል።

አርሶ አደሩ በአንድ ፖሊስ ብቻ ሳይሆን በሁለት ፀጥታ ኃይሎች እንደተደበደቡና በዚህም ምክንያት ግንባራቸው፣ ክርናቸው፣ ጀርባቸው፣ እግራቸውና የባታቸው ጡንቻ መጎዳቱን እንደተናገሩም ቡምላይቭ ዘግቧል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የዕድሜ ባለፀጋ አርሶ አደሮች የምግብ ማዕከል በሚባሉት ፑንጃብና ሃርያና ግዛቶች ለተቃውሞ ወደ መዲናዋ መጥተዋል።

እነዚህ የዕድሜ ባለፀጎች አስለቃሽ ጋዝ ሲረጭባቸው፣ አገሪቱ ውስጥ ያለው አጥንት ሰብሮ የሚገባ ብርድ ባለበት ወቅትም ውሃ ሲርከፈክፋባቸው ማየት በርካቶቸን አሳዝኗል። በሕንድ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገራት ያሉ ሕንዳውያንንም ልብ ሰብሯል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ፣ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ሕንድ ለተቃዋሚ ሰልፈኞቹ የሰጠችው ምላሽ ስጋት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።

አገራቸው "ሁልጊዜም ቢሆን ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን መብት ለመደገፍም ትቆማለች" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት ግን የሕንድን መንግሥት አላስደሰተም። የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የመረጃ እጥረት ያለበትና "መሰረተ ቢስ" ሲሉም አጣጥለውታል።

ሚኒስትሩ ይህንን ይበሉ እንጂ የአርሶ አደሮቹ ተቃውሞ ዓለም አቀፍ ድጋፍን አግኝቷል።

ይህንንም ተከትሎ ባለስልጣናቱ አርሶ አደሮቹ ከመንግሥት ሚኒስትሮች ጋር ውይይት እንዲያደርጉ በሚል በጋበዙዋቸው መሰረት ማክሰኞ እለት የተደረገውም ውይይት ፍሬ አልባ ሆኗል።

ሁለተኛ ውይይትም ሐሙስ እለት ይካሄዳል ተብሏል።

አርሶ አደሮቹ በበኩላቸው በከተማዋ ድንበር በተለያዩ አካባቢዎች መጠለያ የሰሩ ሲሆን ባለስልጣናቱ ይህንን "መጥፎ ሕግ" እስከሚያስቀሩት ድረስ እንቆያለን ብለዋል።

አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት "ለረዥሙ ትግል" ተዘጋጅተው መጥተዋል።

ሩዝ ጨምሮ በርካታ የእህል ክምችታቸውን ጭነው እንዲሁም ምግብ ማብሰያ ብረት ድስትም ሆነ መጥበሻ ይዘን ነው የመጣነው ተብሏል።

አርሶ አደሮቹ እንዳሉት ትግሉ ረዥም ይሆን አይቀርም።