ተዋናይቷ ተቃውሞዋን ለመግለፅ በፈረንሳይ የፊልም ሽልማት ላይ እርቃኗን ወጣች

ኮሪን ማሲየሮ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ፈረንሳዊቷ ተዋናይት ሴዛር ተብሎ በሚታወቀው የአገሪቷ የፊልም ሽልማት ላይ ተቃውሞዋን ለመግለፅ እርቃኗን ወጥታለች።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የአገሪቱ መንግሥት ለባህል ዘርፍ የሚሰጠውን ድጋፍ ችላ ብሎታል። ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልጋልም በማለት ነው ለተቃውሞ ይህንን ያደረገችው።

የ57 አመቷ ኮሪን ማሲየሮ በመጀመሪያ ላይ አህያ የሚመስል ኮትና በደም የተነከረ ቀሚስ ለብሳ የነበረ ሲሆን መድረክ ላይ ከወጣች በኋላ ግን እርቃኗን ቀርታለች።

ማሲየሮ በያዝነው ሳምንት አርብ በተካሄደው የአካል ርቀትን በጠበቀው በዚህ ዝግጅት ላይ በምርጥ አልባሳት ዘርፍ የተዘጋጀውን ሽልማት ለመሸለም ነበር ወደ መድረክ የወጣችው።

ነገር ግን በሰውነቷ ፊት ለፊት ክፍል ላይ "ባህል ከሌለ የወደፊት የለም" የሚለውን ፅሁፍ ለማሳየት እርቃኗን መውጣቷ በርካቶችን አስደንግጧል።

በጀርባዋም እንዲሁ " ጥበባችንን መልሱልን፤ ገንዛባችንን መልሱልን" የሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን ካስቴክስን የሚጠይቅ መፈክርም ፅፋ ነበር።

በወረርሸኙ ምክንያት ሲኒማ ቤቶች ለሶስት ወራት ያህል ተዘግተዋል።

አንዳንድ ተዋናዮችና ዳይሬክተሮችም እንዲሁ በዝግጅቱ ላይ መንግሥት በባህሉ ዘርፍ ሊያደርግ የሚገባውን ድጋፍ ተናግረዋል።

በታህሳስ ወር ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋናዮች፣ የፊልም ዳይሬክተሮች፣ ሙዚቀኞች፣ ተችዎችና በጥበቡ ዘርፍ አሉ የሚባሉ ፈረንሳውያን ፓሪስን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ላይ የተቃውሞ ሰልፎችን አካሂደዋል።

ሰልፎቹ መንግሥት የጥበብ ማሳያ ቦታዎችን መዝጋቱን በመተቸት የተደረጉ ናቸው።

ኮሪን ማሲየሮ

የፎቶው ባለመብት, EPA

በዚህ የሽልማት ወቅት የአልበርት ዶፖንቴል ፊልም የሆነው አዲየው ሌ ኮን ወይም (ደህና ሰንብቱ ጅሎች) የሚለው ፊልም በምርጥነት ተሸልሟል።

አንዲት ህመምተኛ ሴት የጠፋ ልጇን ለመፈለግ የምታደርገውን ፈታኝ ጉዞ የሚያሳየው ሌላኛው ፊልም ሰባት የሴዛር ሽልማቶችን ያሸነፈ ሲሆን በምርጥ ዳይሬክተርነትም ዘርፍ አንዱ ተሸላሚ ሆኗል።

በምርጥ ውጭ አገር ፊልም ዘርፍ የዴንማርኩ 'አናዘር ራውንድ' አሸናፊ ሆኗል።