‘ታግተናል’ ብለው ቤተሰባቸውን ለመዋሸት የሚገደዱት ቻይናውያን ተማሪዎች

እገታ ተፈጸመባቸው ከተባሉ ተማሪዎች አንዷ

የፎቶው ባለመብት, NSW POLICE

የምስሉ መግለጫ, 'እገታ' ተፈጸመባቸው ከተባሉ ተማሪዎች አንዷ

የአውስትራሊያ ፖሊስ እንዳለው፤ ሲድኒ የሚገኙ የቻይና ተማሪዎች በበይነ መረብ አጭበርባሪዎች ኢላማ ተደርገዋል።

ተማሪዎቹ 'ታግተናል' ብለው ቻይና ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃ እንዲልኩ አጭበርባሪዎቹ ያስገድዷቸዋል።

ዘንድሮ ስድስት የበይነ መረብ 'እገታዎች' እንደተከናወኑ ፖሊስ ያስረዳል። ከእነዚህ በአንዱ ታጋችን ለማስለቀቅ 1.43 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏል።

የቤተሰብ አባላቸው እንደታገተ ያመኑ ሰዎች የተጠየቁትን ገንዘብ እንደሚከፍሉ ፖሊስ ገልጿል። ይህ ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣና አጭበርባሪዎቹ በተቀናጀ መንገድ እንደሚንቀሳቀሱም አክሏል።

ተማሪዎች ይህን አይነት ማጭበርበር ሲገጥማቸው ለፖሊስ እንዲያሳውቁም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

ተማሪዎቹ ኢላማ የሚደረጉት እንዴት ነው?

አጭበርባሪዎቹ ከቻይና ኤምባሲ ወይም ከሌላ መሥሪያ ቤት በማስመሰል ለተማሪዎቹ ይደውላሉ። ከዚያም ተማሪዎቹን ቻይና ውስጥ በወንጀል እንደሚፈለጉ ነግረው ያስፈራሯቸዋል።

አጭበርባሪዎቹ አብዛኛውን ጊዜ ማንደሪን (የቻይና ቋንቋ) ይችላሉ። ተማሪዎቹ እንዳይታሰሩ ወይም ከአውስትራሊያ እንዳይባረሩም ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገድዷቸዋል።

ከዚህ በኋላም ተማሪዎቹ ገንዘብ ለማግኘት ሆቴል ተከራይተው፤ ሐሰተኛ የእገታ ቪድዮ አዘጋጅተው ለቤተሰቦቻቸው እና ለጓደኞቻቸው እንዲልኩ ይገደዳሉ።

ኃላፊዎች እንደሚሉት፤ ይህን መሰል ማጭበርበር የሚካሄደው ከአገር ውጪ ስለሆነ ለመቆጣጠር አልቻሉም።

በአንድ ወቅት አንድ አባት ከ1.1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለመክፈል ተገደዋል። ልጃቸው ወዳልታወቀ ቦታ እንደተወሰደች ነበር ያመኑት።

ነገር ግን ለሲድኒ ፖሊሶች ሲደውሉ፤ ከሰዓታት ፍለጋ በኋላ ልጃቸው ምንም ሳትጎዳ ሆቴል ውስጥ ተገኝታለች።

የመርማሪ ፖሊስ ኃላፊው ዳረን ቤኔት “አንዳንድ ቤተሰቦች ቤሳቤስቲን ሳያስቀሩ ያላቸውን ገንዘብ ሁሉ ከፍለዋል” ብለዋል።

ፖሊሶች ጥቆማ ከደረሳቸው በኋላ ተማሪዎቹን የሚያገኟቸው አንዳችም ጉዳት ሳይደርስባቸው ነው።

ብዙ ጊዜ ተማሪዎቹ ሀፍረት ስለሚሰማቸው ወንጀሉን ለፖሊስ አያሳውቁም።

“በበይነ መረብ ለሚከናወን የ‘እገታ’ ማጭበርበር የሚጋለጡ ሰዎች በሚፈጠረው ነገር ተደናግጠው እናገኛቸዋለን። እራሳቸውንም የሚወዷቸውንም ሰዎች ለአደጋ እንዳጋለጡ ይሰማቸዋል” ይላሉ ኃላፊው።

ሰዎች ለምን ይጭበረበራሉ?

ፖሊስ እንደሚለው፤ አጭበርባሪዎቹ ኢላማ የሚያደርጉት የስልክ ቁጥር ማውጫ ዝርዝር (ፎን ቡክ) ላይ ቻይናዊ የአባት ስም ያላቸውን ነው።

የመርማሪ ፖሊስ ኃላፊው ዳረን ቤኔት “ጥቂትም ቢሆን በቀላሉ የሚያጭበረብሩት ሰው ሲያገኙ ትርፋማ ይሆናሉ” ይላሉ።

አውስትራሊያ የሚገኙ የዓለም አቀፍ ተማሪዎች መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት፤ በወረርሽኙ ምክንያት ከመደበኛ የመንግሥት ወዋቅር መገለላቸው ለአጭበርባሪዎች እንዲጋለጡ አድጓቸዋል።

ፖሊስም ዓለም አቀፍ ተማሪዎች መገለላቸው ለወንጀሉ አጋልጧቸዋል ይላሉ።

የመርማሪ ፖሊስ ኃላፊው ዳረን ቤኔት፤ “ተማሪዎቹ ‘ታግተናል’ ብለው ሐሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስል የሚያዘጋጁት በአጭበርባሪዎቹ ሥነ ልቦናዊ ጫና ስለሚደርስባቸው ነው” ይላሉ።

ተመሳሳይ ወንጀል በአሜሪካ እና በኒው ዚላንድም ይፈጸማል።