አውስትራሊያ፡ ኮሜዲያኗን ደፍሮ የገደለው በእድሜ ልክ ተቀጣ

ዩሪዳይስ ዲክሰን

የፎቶው ባለመብት, FACEBOOK

የምስሉ መግለጫ, ዩሪዳይስ ዲክሰን በአውስትራሊያ ተስፋ የተጣለባት ኮሚዲያን ነበረች

አውስትራሊያዊቷ ኮሜዲያን ዩሪዳይስ ዲክሰን ወደቤቷ ስትሄድ ተከትሎ አስገድዶ ከደፈረ በኋላ የገደላት ወጣት የእድሜ ልክ እስራት ተበየነበት።

ጄምስ ቶድ የተባለው የ20 ዓመት ወጣት ወንጀሉን መፈጸሙን ያመነ ሲሆን ባለፈው ዓመት ነበር 22 ዓመቷን ኮሜዲያን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደላት። ወንጀሉም በአውስትራሊያ ትልቅ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።

ጉዳዩን ሲከታተለው ነበረው ፍርድ ቤትም ወንጀሉን ''ሙሉ በሙሉ አረመኔያዊ ተግባር ነው'' ሲል ገልጾታል።

ጄምስ ቶድ ኮሜዲያን ዩሪዳይስ ዲክሰን ከስራ ወጥታ ወደ ቤቷ ስትሄድ ለአንድ ሰአት ያክል የተከተላት ሲሆን 'ሴንትራል ሜልቦርን ፓርክ' በተባለ ጨለም ያለ ቦታ ስትደርስ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞባታል።

ዩሪዳይስ ዲክሰን በአንድ የምሽት ክለብ ውስጥ የኮሜዲ ስራዎቿን አቅርባ ነበር ወደ ቤቷ መሄድ የጀመረቸው። ነገር ግን ያላሰበችው ነገር አጋጥሟት ያሰበችበት ሳትደርስ ቀርታለች።

ጄምስ ቶድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄምስ ቶድ ወደ ፍርድ ቤት ሲገባ

ፍርድ ቤቱ እንዳስታወቀው ጄምስ ቶድ ወደ ባቡር ጣቢያ ከገባችበት ሰአት አንስቶ በትኩረት ሲከታተላት ነበር። በእግሯ የከተማውን ዋና ዋና መንገዶች አቋርጣ ስትሄድም በድብቅ ይከተላት ነበር።

የዩሪዳይስ ዲክሰን ሞት ብዙ አውስትራሊያውያንን ያስቆጣና በሃገሪቱ ስላለው የደህንነት መዋቅር ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳ ነበር።

የአውስትራሊያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዳስታወቀው ደግሞ በሃገሪቱ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በሚያስፈራ ሁኔታ እየጨመሩ መጥተዋል።

ከአምስት ሴት አውስትራሊያውያን አንዷ ጾታዊ ጥቃት አልያም ማስፈራሪያ እንደሚደርስባትም ተገልጿል።