ኤለን መስክ የምድራችን ቀዳሚ ሀብታሙ ሰው ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቴስላ ኤሌክትሪክ መኪና እና የስፔስ ኤክስ የሕዋ ታክሲ ፈጣሪና ባለቤት ኤለን መስክ ባልተጠበቀ ፍጥነት የየዓለም ሀብታሙ ሰው ሆኗል።
መስክ በድንገት 1ኛ የዓለም ሀብታም ሊሆን የቻለው የቴስላ የአክስዮን ዋጋ ማክሰኞ ዕለት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ ሀብቱ ወደ 185 ቢሊዮን ዶላር በመመንደጉ ነው።
ከፈረንጆቹ 2017 ዓ/ም ጀምሮ የዓለም ቢሊዮነሮች ዝርዝርን ከላይ ሆኖ ሲመራ የነበረው የአማዞኑ ባለቤት ጄፍ ቤዞስ ነበር።
የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ኩባንያ ቴስላ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአክስዮን መጠኑ በማይታመን ደረጃ እየጨመረ መጥቶ ትናንት ረቡዕ 700 ቢሊዯን ዶላር እንደደረሰ ተዘግቧል።
ይህ ሁኔታ የኤለን መስክን ሀብት እንዲመነደግ ሳያደርገው አልቀረም። የኤለን መስክ ቴስላ የአክስዮን ፍላጎት ለመጨመሩ በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከነዚህ አንዱ መጪው ዘመን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ብዙ አገራት ፖሊሲያቸው ለኤሌክትሪክ መኪና የሚስማማ መሆኑ አይቀሬ እንደሆነ በመታመኑ ነው።
ቴስላ የኤሌክትሪክ መኪና አሁን ባለው የሀብት ግምት ቁመና ጉዞፎቹ የመኪና አምራቾች ቶዮታ፥ ቮልስዋገን፥ ሀዩንዳይ፣ ጂኤም እና ፎርድ ተሰብስበው ቢደመሩ እንኳ የቴስላን ያህል ዋጋ አይኖራቸውም።
ኤለን መስክ የዓለም ቁጥር አንድ ሀብታም የመሆኑን ዜና በትዊተር ካጋራው አንድ ግለሰብ ሥር "መቼስ የሚገርም ነው" በማለት ስለራሱ ዜና ፈገግ የሚያሰኝ አስተያየት ሰጥቷል። ቀጥል አድርጎም "ዳይ ወደ ሥራ" የሚል ሐሳብ ጽፏል።
ኤለን መስክ ከዚህ ቀደም በትዊተር ሰሌዳው ሀብትን በተመለከተ የጻፈው እንዲህ ይላል።
"የሀብቴ ግማሹ የዓለምን ችግር እንዲፈታ ነው የምፈልገው፣ የተቀረው ግማሹ ደግሞ በማርስ ላይ የተረጋጋ ሕይወት የሚኖርባት ከተማ እንድትፈጠር ነው የምፈልገው፣ መሬት ላይ ለምሳሌ የሰውና የእንሳት ዝርያ ጨርሶ ሊጠፋ ቢችል፣ ለምሳሌ 3ኛው የዓለም ጦርነት ቢፈጠር ወይ እንደ ዳይኖሰር ያለ እንግዳ ፍጥረት ጨርሶ ቢያጠፋን ማርስ ላይ ሕይወት መቀጠል አለበት"
በአሜሪካ ፖለቲካ የዲሞክራቶች የበላይነት ለቴስላ ሀብት መጨመር አንድ ምክንያት ተደርጎ እየተወሰደ ነው። ምክንያቱም ቴስላ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች በመሆኑና ባይደን በመጪዎቹ አመታት በሚወስዷቸው የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች የቴስላ ፍላጎት መጨመሩ አይቀርም የሚል ግምት አሳድሯል።
የኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ እስከ ትናንት ድረስ የቢሊየነሮች ቁንጮ የነበረው የአማዞኑ ቤዞስ ሀብት ሲጨምር ቆይቷል። ምክንያቱ ደግሞ በወረርሽኙ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ ስለነበረ የኦንላይን ግብይት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ነበር።
ሆኖም ግን ቤዞስ ከሀብቱ 4 ከመቶ ፍቺን ተከትሎ ለቀድሞ ባለቤቱ ማኬንዚ ስኮት መስጠቱ የኤለን መስክ ወደ 1ኛ ደረጃ መቆናጠጥ ሌላ ምክንያት ሆኗል።














