የፌስቡክ ዛከርበርግ ሃብት 100 ቢሊዮን ዶላር ገባ

ማርክ ዛከርበርግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማርክ ዛከርበርግ

የፌስቡክ ፈጣሪ ማርክ ዛከርበርግ ሃብት 100 ቢሊዮን ዶላር ገባ።

የዛከርበርግ ሃብት ጣሪያ የነካው አዲስ የተንቀሳቃሽ ምስሎች መጋሪያ ገፅ ያለው ቴክኖሎጂ ኢንስታግራም ላይ ተግባራዊ ካደረገ በኋላ ነው ተብሏል።

አዲሱ ቴክኖሎጂ አነጋጋሪውን የቻይና አፕ ቲክ ቶክን ለመቀናቀን የመጣ ነው ተብሏል።

ረቡዕ ዕለት ፌስቡክ፤ 'ኢንስታግራም ሪልስ' የተሰኘውን አዲስ ቴክኖሎጂ ይፋ አድርጓል። በቀጣዩ ቀን ሐሙስ የፌስቡክ የገበያ ድርሻ በ6 በመቶ ማደጉ ተሰምቷል።

ዛከርበርግ የፌስቡክን 13 በመቶ የገበያ ድርሻ ይቆጣጠራል።

ማርክ ዛከርበርግ፣ የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ እና የማይክሮሶፍት ፈጣሪ የሆነው ቢል ጌትስን በመከተል 'ሴንቲቢሊየነር ክለብ' [ሃብታቸው ከመቶ ቢሊዮን በላይ የሆነ] የተሰኘውን ቡድን ተቀላቅሏል።

የቴክኖለሎጂ ፈጠራ ባለቤቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያካበቱ ባሉት ሃብት ስማቸው የመገናኛ ብዙሃን አፍ ማሟሻ ሆኗል።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትርፋማነታቸው ከጨመረ ድርጅቶች መካከል ፌስቡክ፣ አማዞን፣ አፕልና ጉግል ይጠቀሳሉ። ይህም የሆነበት ምክንያት በርካቶች ቤታቸው በመቀመጣቸው ግብይትም ሆነ የሚፈልጓቸውን ነገሮች በበይነ መረብ አማካይነት በማድረጋቸው ነው።

የዛከርበርግ ሃብት በዚህ ዓመት ብቻ በ22 ቢሊዮን ዶላር ጨምሯል። የአማዞን ፈጣሪ የሆነው ጄፍ ቤዞስ ደግሞ 75 ቢሊዮን ዶላር አፍሷል ሲል ብሉምበርግ አስነብቧል።

ሪልስ የተሰኘው የፌስቡክ አዲስ ቴክኖሎጂ በቻይናውያን ከሚተዳደረው ቲክ ቶክ ጋር ለመቀናቀን የመጣ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ቴክኖሎጂው የፌስቡክ ንብረት በሆነው ኢንስታግራም ላይ የተካተተ አዲስ ገፅ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቲክ ቶክን አግዳለሁ እያሉ በሚዝቱበት ወቅት ይህ ቴክኖሎጂ ይፋ መሆኑ ዛከርበርግ ትርፋም እንዲሆን አድርጎታል ተብሏል።

ቢሆንም ዛከርበርግና ሌሎች ጉምቱ ቢሊየነሮች ኃይላቸው ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ነው ተብለው በአሜሪካና በአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት ይተቻሉ።

አምስቱ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ማለትም አፕል፣ አማዞን፣ አልፋቤት፣ ፌስቡክና ማይክሮሶፍት ያላቸው የገበያ ድርሻ የአሜሪካን ጠቅላላ ምርት 30 በመቶ መሸፈን የሚችል ነው።

የአሜሪካው ሴናተር በርኒ ሳንደርስ ለምርጫ በሚወዳደሩበት ወቅት ፕሬዝደንተ ከሆነ እኒህን ትላልቅ ኩባንያዎች በደንብ እቀርጣለሁ ማለታቸው አይዘነጋም። ሳንደርስ ከቢሊየነሮቹ የሚቀረጠው ገንዘብ መከፍል ለማይችሉ አሜሪካውያን የሕክምና ወጭ ይሆናል ብለው ነበር።

ዛከርበርግ በአንድ ወቅት ከፌስቡክ ድርሻ 99 በመቶውን ለተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች እሰጣለሁ ብሎ ነበር።