በምኒልክ ዘመን የተወለዱት የዓለማችን የዕድሜ ባለጸጋ አረፉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዓለም በዕድሜ ትልቋ የሆኑት ጃፓናዊቷ ካኔ ታናካ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
እማማ ታናካ የተወለዱት እንደ አውሮጳዊያኑ በ1903 ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር በበ1895 ዓ/ም ነበር፡፡
ይህም ማለት ከአድዋ ጦርነት 7 ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡
እማማ ታናካ የትውልድ ዘመናቸው የተረጋገጠና በዓለም በዕድሜ የሚስተካከላቸው እንደሌለ የተመሰከረላቸው አዛውንት ነበሩ፡፡
ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በተወለዱ በ119 ዓመታቸው ነው፡፡
እማማ ታናካ አራት ልጆችን ወልደዋል፡፡
የመጨረሻ ዘመናቸውን ያሳለፉት በጃፓን የአዛውንቶች ክብካቤ ማዕከል ሲሆን ቦርድ ጌሞችን እየተጫወቱ ቼኮሌት እየበሉ አብዛኛውን ጊዜ ያሳልፉ ነበር ተብሏል፡፡
አሁን የርሳቸውን ሞት ተከትሎ በዓለም በዕድሜ ትልቋ ሴት ሩሲል ራንዶን ሆነዋል፡፡
ራንደን ፈረንሳዊት መነኩሲት ሲሆኑ ዕድሜያቸው አሁን 118 ደርሷል፡፡
ፈረንሳዊቷ ራንደን የተወለዱት ቴዎዶር ሩዝቬልት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሳሉ ነበር፡፡
ኤድዋርድ 7ኛ ደግሞ የእንግሊዝ ንጉሥ ነበሩ፡፡ ወይም ደግሞ የራይት ወንድማማቾች የአውሮፕላን ሙከራ ያደረጉበት ዘመን ነበር፡፡
ቱር ዴ ፍራንስ ውድድር የተጀመረውም ያን ጊዜ ነበር፡፡
ጃፓናዊቷ እማማ ታናካ ከዘጠኝ ወንድም እህቶቻቸው 7ኛዋ ልጅ ነበሩ፡፡
ትዳር የመሠረቱት በ19 ዓመታቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ባላቸውን ለመጀመርያ ጊዜ ያዩት በሰርጋቸው ዕለት እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
የእማማ ታናካ ባል በሲኖ ጃፓን ጦርነት ተዋድቀዋል፡፡ ልጃቸው ደግሞ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ተሰልፈዋል፡፡
እማማ ታናካ ከወራት በፊት በተካሄደው የቶክዮ ኦሎምፒክስ ችቦውን እንዲለኩሱ ተመርጠው የነበረ ሲሆን በኮቪድ ምክንያት ግን ያን ሳያደርጉ ቀርተዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2019 እማማ ታናካ የዓለም ቁጥር አንድ የዕድሜ ባለጸጋ መሆናቸውን በሚመሰክር አንድ መርሐግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረው ነበር፡፡
ይሁንና እስከዛሬ ረዥም ዕድሜ በመኖር ረገድ ፈረንሳዊቷን ጄን ሉዊስ ካልመንትን የሚስተካከል አልተገኘም፡፡
እሳቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በፈረንጆቹ በ1997 ዓ/ም ይሁን እንጂ በምድር ላይ የቆዩት ግን 122 ዓመታት ከ164 ቀናት ነበር፡፡
ጃፓን በርካታ የዕድሜ ባለጸጎች የሚኖሩባት አገር ናት፡፡
አሁን የጃፓን የጠቅላላ ሕዝቧ ሲሶው ዕድሜው ከ65 በላይ ነው፡፡
ጃፓኖች ለምን ከሌላው ሕዝብ በተለየ ረዥም ዕድሜ ይኖራሉ ለሚለው ጥያቄ በርካታ መላምቶች ይሰጣሉ፡፡












