በአፍሪካ ቀንድ ሚሊዮኖችን ከረሃብ ለመታደግ ለጋሾች ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ

በኪስማዩ ሶማሊያ የውሃ አቅርቦት የሚቀበሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Ahmed Fais Saed

የምስሉ መግለጫ, በኪስማዩ ሶማሊያ የውሃ አቅርቦት የሚቀበሉ ሰዎች

ለጋሾች በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ በርካታ ሚሊዮኖችን ከረሃብ ለመታደግ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) ምዕራባውያን አገራት እና ለጋሾች ሰዎችን ከረሃብ አደጋ ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት 1.39 ቢሊዮን ዶላር ለመስጥት ቃል መግባታቸውን አስታውቋል።

የአሜሪካ መንግሥት ለድርቁ ምላሸ የሚሆን 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደርጋለሁ ሲል፣ የካናዳ መንግሥት ደግሞ 73 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብቷል።

ይህ የምዕራባውያን ድጋፍ የተደረገው በኢትዮጵያ፣ በኬንያና ሶማሊያ ሚሊዮኖችን ከረሃብ ለመታደግ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ከቀረበ በኋላ ነው።

ከ40 በላይ የሚሆኑት እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የከፋ አደጋ ከመከሰቱ በፊት በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙት አገራት ሚሊዮኖችን ከረሃብ ለመታደግ ርብርብ እንደሚደረግ ያሳወቁት ከትናንት በስቲያ ሰኞ ሚያዚያ 17/2014 ዓ.ም. ባወጡት የጋራ መግለጫ ነው።

ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ 14 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን እና አስፈላጊው ድጋፍ የማይደረግ ከሆነ የተጎጂዎች ቁጥር ወደ 20 ሚሊዮን ሊያሻቅብ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይህን ማሳሰቢያ ያወጡት የአውሮፓ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በአፍሪካ ቀንድ ስለተከሰተው ድርቅ ማክሰኞ ሚያዚያ 18/2014 ዓ.ም. ውይይት ከማድረጋቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።

ትናንት በጄኔቭ በተደረገው ውይይት ላይ የሶማሊያ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ መንግሥታት ተወካዮች ተገኝተዋል ተብሏል።

ግብር ሰናይ ድርጅቶች ምዕራባውያን አገራት ለመስጠት ቃል በገቡት ገንዘብ ተጎጂ ለሆኑ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እና መድኃኒት አቅርቦት ሥራዎችን እንደሚሠሩ፤ የቤት እንስሳት መኖ እና መድኃኒት እንደሚሰጡም ኦቻ አስታውቋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እአአ 2020 ማብቂያ ላይ የረሃብ አደጋ የተጋረጠባቸው ሰዎች ቁጥር ከ14 ሚሊዮን ወደ 20 ሚሊዮን ከፍ ሊል ይችላል ሲል ከዚህ ቀደም ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሕይወት አድን ሥራዎችን ለመሥራት 4.4 ቢሊዮን ዶላር ጠይቀዋል።

በድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት የተጋለጡት በሚሊዮን የሚቆጠሩት የአፍሪካ ቀንድ ነዋሪዎች፤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በግጭት፣ በአንበጣ መንጋ እና አሁን ደግሞ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ በሸቀጦች ዋጋ መናር ምክያት ውስብስብ ችግር ውስጥ ገብተዋል።