‘ድንግልና የሚሰጥም የሚወሰድም ነገር አይደለም’

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ድሮ በበርካታ ማኅበረሰቦች ዘንድ ለአቅመ አዳም እና ሔዋን የደረሱ ወጣቶች ከጋብቻ በፊት የግብረስጋ ግንኙነት እንዳያደርጉ እና ድንግል ሆነው እንዲቆዩ ይጠበቃል።
ይህም በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ልማድ ነው። በተለምዶ የሰርግ ቀን ሙሽሪት ድንግልና አላት ከተባለ 'ክብሯን እና ንጽህናዋን' ጠብቃ የቆየች በሚል ደስታ ይሆናል።
ይህም ለወላጆቿም ሆነ ለእርሷ የክብር መገለጫ ነው። ማኅበረሰቡም እርሷንና ቤተሰቦቿን በዜማ እያሞካሸ፣ የትዳር አጋሯን 'ወንድነት' እያደናነቀ፣ የ'ድንግልናዋን' ደም በነጭ ጨርቅ በማድረግ ለሰርጉ እድምተኛ በማሳየት ይጨፍራሉ፤ ይበላሉ ይጠጣሉ።
በተቃራኒው ሴት ልጅ ድንግልና የላትም ከተባለ፣ እንድታፍር፣ እንድትገለል፣ ክብሯን ጠብቃ ቆይታለች ከተባለችው በተለየ ዓይን እንድትታይ ይሆናል።
ሌሎች የማናውቃቸው መገለሎች እና ጥቃቶችም ሊደርስባት ይችላል።
ይህ ልማድ እስካሁን ዘልቆ "ድንግልናዋን ለእከሌ ሰጠችው፤ ድንግልናዋን እርሱ ነው የወሰደው የሚል ወሬ አሁን ድረስም በወዳጅ ጓደኞቻችን ዘንድ የሚወራ ጉዳይ ነው" ይላሉ ዶ/ር ቤርሳቤህ መካሻ።
እውን ድንግልና የሚሰጥ ነገር ነው?
ይህንን ጥያቄ ከመመለስ በፊት ድንግልና ምን እንደሆነ ለማወቅ እንዲሁም ስለዚህ ጉዳይ የሚነገሩ እውነት እና ሐሰተኛ ነገሮችን ዶ/ር ቤርሳቤህ መካሻ ነግረውናል።
ዶ/ር ቤርሳቤህ የሕክምና ዶክተር ሲሆኑ፣ በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ አስተምረዋል። በጾታ እና በሥነተዋልዶ ጤና ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ላይ የሚሰሩት ዶ/ር ቤርሳቤህ በአሁኑ ወቅት በዩኬ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማኅበረሰብ ጤና ሥነተዋልዶ ላይ እየሰሩ ነው።
እኚህ የሕክምና ባለሙያ ድንግልና በማንኛውም ጉዳይ ላይ አንድን ተግባር አለመፈፀምን የሚያሳይ ቃል ነው ይላሉ። ስለዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድን ነገር ስንፈጽም ድንግልናችንን እንደማጣት ሊቆጠር ይችላል ሲሉም ያብራራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወደ ግብረ ስጋ ግንኙነት ስናመጣው ደግሞ፣ አንድ ሰው ግብረ ስጋ ግንኙነት ወይንም ደግሞ ወሲብ ፈጽሞ የማያውቅ ከሆነ 'ድንግል' ሊባል ይችላል።
ከዚህ በፊት ድንግልና በተለያየ ባህል ውስጥ በተለያየ መንገድ ሊገለጽ ይችላል።
ለምሳሌ በተለምዶ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ሴቶች ከዚህ በፊት ግብረ ስጋ ፈጽመዋል፣ አልፈጸሙም የሚለውን ለማወቅ የብልታቸውን ጫፍ ወይንም ደግሞ በር ሸፍኖ የሚገኝን አካል መኖር አለመኖሩን በወሲብ ወቅት በመፈተሽ ድንግል መሆን አለመሆኗን ለማወቅ ይሞከራል ይላሉ።
የሕክምና ባለሙያዋ፣ ድንግል መሆን ለሴትም ለወንድም ከዚህ በፊት የግብረ ስጋ ግንኙነት ልምድ አለመኖር ሲሆን፣ በተለይ ለሴቶች 'ሃይመን' በጣም ስስ የሆነ ቲሹ ነው ይላሉ።
ስለዚህ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ድንግል ስንል የእንግሊዘኛውን 'ሃይመን' በአቻነት መጠቀማችንን ልብ ይሏል።
ሴቶች ከዚህ የአካል ክፍል ጋር ለምን ይወለዳሉ ለሚለው ጥያቄ የተለያየ አከራካሪ መልስ ቢኖርም ሴት ሕጻናት ሲወለዱ፣ በፊንጢጣ እና በብልታቸው ቀዳዳ ተቀራራቢ በመሆኑ፣ ዓይነምድር ወደ ብልታቸው ተመልሶ እንዳይገባ የሚከላከል የአካል ክፍል ነው የሚል መላ ምት አሉ ሲሉ ይናገራሉ።
ዶ/ር ቤርሳቤህ ይህ ድንግልና የተሰኘ የሴት ብልት አካል በተለያየ ቅርጽ ሊፈጠር እንደሚችል ያስረዳሉ።
"በተወሰኑ ሰዎች ላይ በጣም ትንሽ ቲሹ ሊሆን ይችላል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ከእነ አካቴው ላይኖር ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ የሴት ብልትን ቀዳዳ ሙሉ በሙሉ ሊሸፍን ይችላል" ብለዋል።
በዚህ ሁኔታ ይህ ድንግልና የተሰኘ የሴት ብልት አካል ሳይኖራቸው የሚወለዱ ሴቶች፣ ከዚህ በፊት ወሲብ መፈፀም አለመፈፀማቸውን በአካላቸው ማረጋገጥ አይቻልም ማለት ነው ሲሉ ያክላሉ።
ይኹን እንጂ ይህ ድንግልና የተባለው የብልት አካል ሲኖር፣ የግብረ ስጋ ግንኙነት በሚፈፀምበት ወቅት የወንድ ብልት ስለሚገፋው ሊደማ፣ ሊያም እና ሊቀደድ ይችላል።
ድንግልና ሴት ለወንድ ልጅ የምትሰጠው ነገር ነው?
ሰዎች ከዚህ በፊት የግብረ ስጋ ግንኙነት አድርገው እንደማያውቁ ሲናገሩ እና ለመጀመሪያ ከእገሌ ጋር ወይንም ከእገሊት ጋር ነው ይህንን ጉዳይ የፈፀምኩት ሲሉ በስነተዋልዶ ቋንቋ የመጀመሪያ የወሲብ ሕይወታቸውን ምዕራፍ [sexual debut] ጀመሩ ማለት ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ መልኩ ወንድም ሆነ ሴት የመጀመሪያ የወሲብ ተሞክሮ በግል፣ አንዳንዴም እንደ ምስጢር የሚይዙት ስለሆነ ትልቅ ስፍራ የሚሰጡት መሆኑን ያብራራሉ።
በተለይ ሴቶች "ድንግልናቸውን ለወሰደ ሰው የተለየ ቦታ አላቸው የሚባለው፣ የማኅበረሰብ ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ቢሆንም እስከ አሁን በማውቀው የጤና ጥናት ግን ድንግልና የተባለውን የብልት አካልን በማጣት እና በአእምሯችን መካከል ያለ ግንኙነት እንዳለ የሚያሳይ ነገር መኖሩን አላየሁም" ይላሉ።
"ስለዚህ ስለ ድንግልና የተባለው አካል ስናወራ የሚሰጥም የሚወሰድም ነገር የለም። ግብረ ስጋ ግንኙነት በሚፈፀምበት ወቅት የሚያጋጥም ተፈጥሯዊ ሂደት ነው።"
ድንግልና ያለ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ሊጠፋ ይችላል?
ዶ/ር ቤርሳቤህ እዚህ ጉዳይ ላይ በመጀመሪያ መረዳት ያለብን ይላሉ "ሴቶች ከዚህ የአካል ክፍል ጋር ላይወለዱ እንደሚችሉ ነው።"
በሌላ መንገድ ደግሞ ይህ ድንግልና በጣም ስስ የብልት አካል ስለሆነ አንዳንዴ ግብረ ሥጋ ተፈጽሞ ምንም ዓይነት መድማት ሳይኖር ሊያልፍ ይችላል በማለት ያብራራሉ።
ይኹን እንጂ በስፖርት እና በተለያዩ አደጋዎች ወይንም እንቅስቃሴ ምክንያት ሊደማ እና ሊቀደድ ይችላል ይላሉ።
ስለዚህ ይህ አካል በተለያየ ቅርጽ ከመኖር ባሻገር አንዳንዴ ፈጽሞ ላይኖር፣ በተለያየ ምክንያት ደግሞ ሊጠፋ ይችላል።
ነገር ግን በባህላችን ሴት ከዚህ በፊት የወሲብ ማድረግ አለማድረጓን ለማወቅ የሚሞከረው በዚህ የብልት አካል መኖር አለመኖር ስለሆነ ድንግናዋን አጣች ሲባል ልንሰማ እንችላለን ይላሉ።
ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ግብረ ስጋ ሲያደርጉ ሕመም ይሰማቸዋል?
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ወሲብ ሲፈጽሙ ሕመም የሚሰማቸው የብልታቸው ጡንቻ ጠንካራ ስለሆነ ነው።
ይህንንም ሲያብራሩ ሰውነታችን አዲስ ልምምድ ውስጥ እያለፈ ስለሆነ ነው ይላሉ።
ስለዚህም ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ወሲብ ሲፈጽሙ ሕመም እንዲሰማቸው የሚያደርገው፣ ድንግልና የተባለው የሴት ብልት አካል በወንድ ብልት በመገፋት ከሚመጣ ሕመም ይልቅ የሴት ብልት አለመፍታታቱ እንደሆነ ያብራራሉ።
ሆኖም ግን ድንግል የተባለው የሴት ብልት አካል በተለያየ ቅርጽ ስለሚኖር ሕመም ሊሰማ ይችላል።
ለምሳሌ "አንዳንድ ድንግልና የሴት ብልት ቀዳዳን ሙሉ በሙሉ ስለሚሸፍን ምንም ዓይነት ቀዳዳ ሳይኖር ይቀራል። ይህም ሴቶች በወር አበቡ ዑደት ወቅት መፍሰስ ሳይችል እስከመቅረት ሊደርስ ይችላል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ እንዲያውም የቀዶ ሕክምና እርዳታ ሊያስፈልግ የሚችልበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል" በማለት ያብራራሉ።
ሴቶች ድንግል ሆነው ሊያረግዙ ይችላሉ?
"በመጀመሪያ ድንግልና የሴት ብልት አካል እያለ ማርገዝ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ጉዳይ አይደለም" ይላሉ ዶ/ር ቤርሳቤህ።
ይኹን እንጂ "አንዳንድ የድንግልና ቅርጾች የወንድ ብልት ወደ ሴት ብልት ሳይገባ የዘር ፍሬው ውጪ ላይ ፈስሶ ካለ፣ ወደ ውስጥ እንዲገባ ሊያደርግ ወይንም ሊፈቅድ ይችላል። በዚህ ጊዜ ሴቲቱ ድንግል ሆና ልታረግዝ የምትችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ማለት ነው።"
"በሌላ በኩል ደግሞ ድንግልና እንደሌላው የሰውነታችን አካል ተቆርጦ ከደማ በኋላ ሊድን እና ወደ ቀድሞ ቦታው ሊመለስ ይችላል" የሚሉት ዶ/ር ቤርሳቤህ ይህ በተለይም በተደጋጋሚ ግብረ ስጋ ካልተፈፀመ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ይህ በሚሆንበት ጊዜ አንዲት ሴት ለመውለድ ሆስፒታል ስትሄድ ድንግልና የተባለው የብልት አካል እንደነበረ ሊገኝ ይችላል።
በዚህ ሁኔታ በተለያየ ማኅበረሰብ ዘንድ ድንግልና ትልቅ ቦታ ስለሚሰጠው የሕክምና ባለሙያዎቹ ይህንን 'በመጠበቅ ወይንም በማክበር' ልጁን በቀዶ ሕክምና እንድትገላገል የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ ይላሉ።
ስንት የድንግልና ዓይነቶች አሉ?
ዶ/ር ቤርሳቤህ ይህ በሴት ብልት ጫፍ (በር) ላይ የሚገኝ አካል የተለያየ ቅርጽ ስላለው፣ የሁሉም ሴቶች ላይመሳሰል እንደሚችል ይገልጻሉ።
ይኹን እንጂ "ብዙ ጊዜ የሴት ብልት ቀዳዳን እስከ ግማሽ ድረስ የሚሸፍን ሆኖ፣ የወር አበባ የሚፈስበትን ቀዳዳ የሚተው ተፈጥሮ ነው። ከዚህ ውጪ ግን የሁሉም ሴቶች ድንግልና አይመሳሰልም።"

የፎቶው ባለመብት, Prashanti Aswani
ድንግልናን መልሶ ማግኘት ይቻላል?
ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአረብ አገራት በጋብቻ ወቅት ሴቶች ድንግል ሆነው እንዲገኙ ይጠበቃል።
ትልቅ ክብር የሚሰጠውም ጉዳይ ስለሆነ የሕክምና ባለሙያዎች መልሰው ይህንን አካል ለመተካት ሲሞክሩ ይታያል ሲሉ ያብራራሉ።
ይኹን እንጂ ይህ የባሕል ጉዳይ እንደሆነ የምንረዳው አደጉ በሚባሉት አገራት፣ ሰዎች ድንግልናቸውን ይዘው የሚጠብቁት ነገር ሳይሆን በሕይወታቸው ቶሎ ማለፍ ያለበት እርከን አድርገው ነው የሚያዩት ይላሉ።
የድንግልና ምርመራ ምንድን ነው?
ከጋብቻ በፊት ግብረ ሥጋ ግንኙነት ሳያደርጉ መቆየት የግል ውሳኔ ቢሆንም "ማኅበረሰቡ ሴቶች ላይ በሚያደርገው ጫና ግን በተለያየ ማኅበረሰብ ውስጥ አንዲት ሴት ወሲብ መፈፀም አለመፈፀሟን ለማወቅ የሕክምና ምርመራ በማድረግ ለማረጋገጥ ሲሞከር ይታያል" ይላሉ።
ይህ ግን የሴትን የግል መብት የሚጋፋ እና በተባበሩት መንግሥታት ጭምር በተለያዩ አገራት ውስጥ የተከለከለ መሆኑን ይናገራሉ።
ልክ አንድ ወንድ፣ ከዚህ በፊት ወሲብ መፈፀም አለመፈፀሙን በምርመራም ሆነ በሌላ መንገድ ለማረጋገጥ እንደማይቻለው እና እነደማይጠየቀው ሁሉ አንዲት ሴትም ይህ የግል ጉዳይዋ ስለሆነ፣ በራሷ ፍላጎት ካልተናገረች በቀር፣ በምንም መንገድ ለማረጋገጥ መሞከር መብቷን ይገፋል ይላሉ።
ዶ/ር ቤርሳቤህ እንደሚሉት ከሆነ ከድንግልና ጋር የሚገናኙ ጉዳዮች፣ የሚነገሩ ሃሳቦች ከእምነት፣ ከባህል እና የተለያየ የማህበረሰብ እሳቤ የመነጨ እንጂ ይህ ድንግልና ከተባለው ስነ ሕይወታዊ ከሆነው እና ሰውነታችን ላይ ከሚገኘው ክፍል ጋር የተገናኘ አይደለም።












